‹‹ተመርቄ ሥራ ስቀጠር የመጀመሪያ ደመወዜን ሙሉ ለሙሉ ለእናቴ ነው የምሰጣት፤›› ያለው የ21 ዓመቱ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዳንኤል ደጀኔ ነው፡፡
ዳንኤል የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ወጣቱ የትምህርት ወጪውን ለመሸፈን ክረምት ክረምቱን የአስተናጋጅነት ሥራውን በላፓሪዚያን ካፍቴሪያ ይሠራል፡፡
‹‹የእኔ ስኬት በስሬ ያሉትን ሰዎች እንደፈለጉት ማኖር ስችል ነው፤›› የሚለው ዳንኤል፣ ሁለት ወንድሞቹን ጨምሮ አምስት የቤተሰቡን አባላት የኢንጂነሪንግ ትምህትቱን ሲጨርስ አሁን ካሉበት ችግር ማላቀቅ ያልማል፡፡
‹‹አሁን ላይ አስተናጋጅ ነኝ፡፡ የማስተናገድ ሥራን የምሠራው ግን በዓመት ለሁለት ወር ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቀሪውን የዓመት ጊዜ በትምህርት ላይ ነው የማሳልፈው፤›› ያለው ዳንኤል፣ የሚማረው ትምህርት ውጤታማ እንዲሆን ረድቶት የሕይወት ግቡን እንደሚያሳካ ተስፋውን ይናገራል፡፡
ዳንኤል የማስተናገድ ሥራን የጀመረው የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር፡፡ በወቅቱ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት አባቱ ሥራ ስላልነበራቸው፣ ከእርሳቸው ጋር አብሮ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሥራ ማፈላለግ ይጀምራሉ፡፡ አባቱ መንገድና ትራንስፖርት ሲቀጠሩ፣ ዳንኤል ደግሞ ሰው አመቻችቶለት በላፓሪዚያን ካፍቴሪያ አስተናጋጅ ይሆናል፡፡
ከሚኖርበት ገደብ አሳሳ (በባሌና በአርሲ ድንበር ላይ የምትገኝ ከተማ) የቀን ሥራ ለመሥራት አቅዶ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ዳንኤል፣ በላፓሪዚያን ካፍቴሪያ የመቀጠር ዕድሉን ሲያገኝ ደመወዙ 150 ብር ነበር፡፡ ‹‹የማስተናገዱን ሥራ በጀመርኩበት በመጀመሪያው ቀን የ30 ብር ጉርሻ ሳገኝ በጣም ተደስቼ ነበር፤›› ያለው ዳንኤል፣ በአንድ ቀን ያገኘው 30 ብር ቤተሰቡ ካለበት የገንዘብ ችግር ጋር ሲያነጻጽረው ሥራው ጥሩ ተስፋን እንደሰጠው ተናግሯል፡፡
ዳንኤል የ10ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤቱ 3.2 ሆኖ ስላለፈ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አሳሳ ተመለሰ፡፡ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ባለው ክረምትም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በመምጣት እዚያው ላፓሪዚያን ማስተናገዱን ቀጠለ፡፡
የክረምት ዕረፍቱን እየጠበቀ ወደ ካፍቴሪያው እየመጣ የሚያስተናግደው ዳንኤል፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 328 ነጥብ አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላም ክረምቱን እየመጣ ማስተናገዱን ግን አላቋረጠም፡፡
በአሁኑ ሰዓት የ230 ብር ደመወዝተኛ የሆነው ይህ ወጣት፣ የሚያገኘውን ደመወዝ ከነጉርሻው እያስቀመጠ (ከዚያም ላይ አንዳንዴ ቤተሰቡን እየረዳ) ትምህርቱን ይማርበታል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ቤተሰቡ አንድ ከብት ሸጦ ካገኘው ገቢ 400 ብር አንዴ ብቻ የተላከለት ዳንኤል፣ ጓደኞቹ በየወሩ 700 ብር ሲላክላቸው ስሜቱ እንደማይጎዳና አንዳንዴም እነዚህ ጓደኞቹ ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ተናግሯል፡፡
‹‹በማስተናግድበት ሰዓት ዩኒቨርሲቲ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ሲያገኙኝ የማሾፍ ነበር የሚመስላቸው፤›› ያለው ዳንኤል፣ የትምህርት ጓደኞቹ እንደሚያስተናግድ ሲያውቁ የሚያስተናግዳቸው ደንበኞቹ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ እንደሚማር ሲያውቁ ሁኔታው ያልተለመደ በመሆኑ መጀመሪያ ተገርመው ከዚያ በኋላ ግን እንደሚያበረታቱት ተናግሯል፡፡
ባሌ ሮቤ የተወለደው ዳንኤል፣ አባቱ ለሥራ እየተቀየሩ በሄዱባቸው ቦታዎች በሙሉ (ገደብ አሳሳ፣ አደሌ፣ ሮቤ፣ ነቀምት) አብሮ ከቤተሰቡ ጋር እየሔደ ተምሯል፡፡
ወጣቱ ተመርቆ ሥራ ሲይዝ የቤተሰቡ ታሪክ እንደሚቀየር ያምናል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ምንም ሳያማርር የማስተናገድ ሥራውን እየሠራ ትምህርቱን ጥግ እንሚያደርስ፣ ከዚያም ቤተሰቡን እንደልብ እንደሚያኖር ተስፋውን ተናግሯል፡፡
ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።
ተጻፈ በ ምዕራፍ ብርሃኔ, EthiopianReporter.com
yes
i hope this will be informative website so far