የስምንት ባለሀብቶች የሕይወት ታሪክ

downloadዳንኤል ክብረት

መምህሩ ናቸው፤ የእነዚህን ባለሀብቶች የሕይወት ታሪክ ሥሩ ብለው የሰጡን፡፡ ስምንት ባለ ሀብቶች፡፡ እነዚህን ሰዎች የምናውቃቸው በቴሌቭዥን እየቀረቡ ስለ ልማት ሲናገሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ተሸልመዋል፡፡

እኛ መምህራችንን ጠየቅናቸው፡፡ እነዚህን ለምን መረጧቸው? ስንል፡፡ እርሳቸውም ‹‹እነዚህን በሦስት መመዘኛ መረጥኳቸው›› አሉ፡፡

‹‹አንደኛ ልማታውያን ናቸው፣ ሁለተኛ ተሸላሚ ናቸው፣ ሦስተኛ ደግሞ ዛሬ ቢጠሯቸው የማይሰሙ የናጠጡ ባለጠጎች ናቸው፡፡›› አሉ መምህራችን፡፡

‹‹ስለዚህም ወጣቱ ትውልድ ከእነርሱ ትምህርት መቅሰም አለበት፡፡ ሀብት እንዲሁ አይገኝም፡፡ ተለፍቶ ነው፤ ተደክሞ ነው፡፡ ደም ተተፍቶ ነው፡፡ ‹ፐ› ላይ ለመድረስ ከ‹ሀ› መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ከዕንቁላል ንግድ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከሱቅ በደረቴ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከአንዲት ሱቅ ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ ከጉልት ተነሥተው ሚሊየነር የሆኑ አሉ፡፡ እነዚህ ለትውልዱ አርአያ ናቸው›› አሉን መምህሩ፡፡

ስምንት ቡድን ተቋቋመ፡፡ ስምንቱ ቡድኖች አንዳንድ ሚሊየነር ያዙ፡፡ ታሪካቸውን የምንሠራበት ቅጽ ተሰጠን፡፡ የመጀመሪያዋን ብር እንዴት አገኟት? ወደ ሚሊየነርነት በየት መንገድ ተጓዙ? ምን ዓይነት ውጣ ውረዶችን አለፉ? እያንዳንዷን ሀብት እንዴት አጠራቀሟት? የሚሉ ጥያቄዎች ተሰጡን፡፡

እኛም የደረሱንን ባለሀብቶች እያነሣን ‹የኛ ባለሀብት ምርጥ ታሪክ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ እንዲህ እና እንዲያ ሰምተናል እያልን እንፎካከር ጀመር፡፡ በቡድን የተሰጠኑንን ባለሀብቶች ታሪክ ሠርተን ከሁለት ሳምንት በኋላ ለመገናኘትና የደረስንበትን ለመወያየት ተቀጣጥረን ተለያየን፡፡

ከሁለት ሳምንት በኋላ በመወያያ ክፍላችን ስንገናኝ ሁላችንም ፈገግታችንን ለባለሀብቶቹ ሽጠንላቸው የመጣን ይመስል እንዳኮረፍን ነበርን፡፡ ሁሉም እንደ ነፋስ አቅጣጫ መጠቆሚያ ራሱን ይወዘውዛል፡፡ መምህራችን እስኪመጡ ድረስ የረባሽ ስም ይጻፋል የተባልን ይመስል ዝም እንዳልን ነበር፡፡

መምህሩ መጡና ‹በሉ የደረሳችሁበትን አቅርቡ› አሉን፡፡ ሁሉም ዝም አለ፡፡ ‹‹የቤት ሥራችሁን አልሠራችሁም ማለት ነው?›› አሉን፡፡ ዝም፡፡

የመጀመሪያውን ቡድን ጠሩ፡፡ ልጀቹ ወጡ፡፡ ‹‹እኛ ያገኘናቸው ባለሀብት ምንም ነገር አልነበራቸውም፡፡ የሀብት ማግኛ መንገዳቸውም ‹ማመቻቸት› ይባላል፡፡ድንገት አንድ ዘመዳቸው ከአንድ ድርጅት በርካሽ የግንባታ ማሽነሪዎችን እንዲገዙ አመቻቸላቸው፡፡ ማሽነሪዎቹንም ለመግዛት ከባንክ ብድር ተመቻቸላቸው፡፡ ብድሩንም ለመውሰድ ኳላተራል ተመቻቸላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ በአንድ ጊዜ በሁለት እጅ የማይነሡ ባለሀብት ሆኑ፡፡›› ‹‹እሺ ከድህነት እንዴት ነው ወደ ባለሀብትነት የተለወጡት፣ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር›› ‹‹ምንም ሂደት የላቸውም፡፡ በድንገት ተነሡ፤ በድንገት አደጉ፤ በድንገት ተመነደጉ››

‹እሺ እናንተስ› አሉ ወደ ሁለተኛው ቡድን ዞረው፡፡ ልጆቹ ተነሡ፡፡ ‹‹የኛ ባለሀብት ምንም ነበሩ፡፡ የሀብት መንገዳቸውም ‹ማስገባት› ይባላል፡፡ ድንገት አንድ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንጻ ሲሠሩ ታዩ፡፡ ምንድነው ተብሎ ሲጣራ ሚስታቸው የእነ እንትና ዘመድ ናቸው አሉ፡፡ እንዴው አንድ ቀን ነው አሉ፡፡ መኪና ሙሉ ሞባይል ጭነው ከሐርቲሼክ አዲስ አበባ የገቡት፡፡ ፈታሾቹም ምን አፍዝ አደንግዝ እንደተደገመባቸው አይታወቅም እንደ ኤድስ ማስታወቂያ አላየንም አልሰማንም ብለው አሳለፏቸው፡፡ ይሄው ሚሊየነር ሆኑ››

‹እናንተስ›› አሉ ገርሟቸው ሦስተኛዎቹን ቡድኖች ‹‹የኛ ባለሀብት ደግሞ ንክኪ ናቸው ይባላል፡፡ ሳይነካኩ በፊት ግንበኛ ነበሩ፡፡ ከተነካኩ በኋላ ግን በሞቱ ሰዎች ስም ሳይቀር መሬት እየወሰዱ ቸበቸቡት፡፡ አሁን ስለ መሬት ፍትሐዊ አጠቃቀም ትምህርት የሚሰጡ የሪል ስቴት ባለሀብት ሆነዋል፡፡ ከቀበሌ ቤት ወጥተው ቀበሌ የሚያህል መሬት ወስደው ለቀበሌ ደንብ ማስከበር የሚያስቸግር የሀብታም ቀበሌ የሚሆን ሪል ስቴት እየገነቡ ነው፡፡ ይኼው ነው›› አለ የቡድኑ መሪ፡፡

አራተኛው ቡድን ተነሣ፡፡ ‹‹የኛው ለየት ይላሉ፡፡ የሀብት ማግኛ መንገዳቸውም ‹መጠጋት› ይባላል፡፡ ከአንድ ሀብታም ሰው ጋር አንድ ወዳጃቸው ያገናኛቸዋል፡፡ የእርሳቸው ሥራ ሀብታሙ ሲያዝን እርሳቸው ማልቀስ፣ ሀብታሙ ሲስቅ እርሳቸው መንከትከት፣ ሀብታሙ ሲያመው እርሳቸው መርፌ መወጋት፣ ሀብታሙ ሲሸተው እርሳቸው ማነጠስ፣ ሀብታሙ ሲናደድ እርሳቸው መደባደብ ብቻ ሆነ፡፡ ከዚያም እርሳቸውም ሳያስቡት፣ ኧረ እንዲያውም ሳያውቁት ሚሊየነር ሆነው ተገኙ፡፡

አምስተኛው ቡድን ቀጠለ፡፡ ‹‹እኒህኛው ባለሀብት ‹መሰጠት› በተባለው መንገድ ነው ሀብት ያገኙት፡፡ ምን ነገር አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን በአንድ ባለ ሥልጣን አማካኝነት እኔ ነኝ ያሉ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይሰጧቸው ጀመር፡፡ ቢወዳደሩም ያልፋሉ፤ ባይወዳደሩም ያልፋሉ፡፡ እንኳን የመንግሥት የኤን ጂ ኦ ፕሮጀክቶችም ይሰጧቸዋል፡፡ እነሆ በዚህ መንገድ ዛሬ የሀገሪቱ ወሳኝ ባለሀብት ሆነዋል››

ስድስተኛው ቡድን ተከተለ፡፡ ‹‹የኛ ባለሀብት የሀብት መንገድ ‹ብቻ› ይባላል፡፡ አንድን ዕቃ ለማስገባት የሚፈቀድላቸው ‹እነ እገሌ ብቻ› ናቸው፡፡ ስለዚህም በፈለጉት መንገድ የፈለጉትን ዓይነት ዕቃ ያስገባሉ፡፡ በፈለጉት ዋጋም ይሸጣሉ፡፡ መመሪያቸው ብትፈልግ ግዛ ባትፈልግ ተወው ነው፡፡ እኒህ ባለ ሀብት ከዐሥር ዓመታ በፊት አንዲት የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ብቻ ነበረቻቸው፡፡ በአንድ እርሳቸውም በማያስታውሱት ቀን ግን የሆነ ዕቃ ‹ብቸኛ አስመጭ› እንዲሆኑ ተሾሙ፡፡ ተሾመውም አልቀሩ ይኼው ሚሊየነር ሆኑ፡፡

‹ሰባተኛውስ ቡድን› አሉ መምህሩ ‹‹የኛው ሰው የሀብት መንገድ ‹ትብብር› ይባላል፡፡ እርሳቸው መርካቶ ሱቅ ከፍተው ከዱባይ ዕቃ ያመጡ ነበር፡፡ እንድ ባለ ሥልጣን ግን ‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ረዳት እንፍጠርልዎ› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ተስማሙ፡፡ ረዳት የመንግሥት ባለ ሥልጣንም ተፈጠረላቸው፡፡ ከእርሱም ጋር ሸሪክ ሆኑ፡፡ እነሆም መንገዱን እርሱ ሲጠርግ ሥራውን እርሳቸው እየሠሩ ባለሀብት ተባሉ፡፡ ጉድ ነው ዘንድሮ አሉ መምህሩ፡፡

ስምንተኛው ቡድን ቀጠለ፡፡ ‹‹የዚህኛው መንገድ ‹ቀንዶ› ይባላል፡፡ ባለ ሀብቱ ከብት እያረዱ በመሸጥ ይታወቃሉ፡፡ አንድ ሰው ግን ከብት እዚህ ከምትሸጥ ለምን ድንበር ሄደህ አትሸጥም አላቸውና፡፡ ወሰዳቸው፡፡ የሀገሪቱንም የቀንድ ከብቶች ድንበር እያሻገሩ ሶማሌና ሱዳን መላክ ጀመሩ፡፡ ሰውም ቀንዶ ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ቀንዳም ባለሀብት ሆነዋል፡፡

መምህሩ ተነሡና አፈጠጡብን፡፡ ‹እና ታሪካቸው ይኼ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ አልፈው፣ እንዲህ ሆነው፣ ይህን ተፈትነው፣ ይህንን ውጣ ውረድ አልፈው፣ ይህን ልምድ ቀስመው የሚባል ታሪክ የላቸውም ማለት ነው?›› አሉ መምህሩ፡፡ አንዱ ጓደኛችን ተነሣና ‹‹አዎ፤ ሀብት እንጂ ታሪክ የላቸውም፡፡ ሀብታቸው ድንገቴ ነው፡፡ በቃ ድንገት ተነሥተው እንደ ሮኬት ተተኮሱ፡፡ በቃ፡፡ ከአንድ ቀጥለው ሚሊየን ነው የቆጠሩት፡፡››

‹‹ታድያ እንዴት ነው ለእናንተ አርአያ የሚሆኑት›› አሉ መምህሩም ተናደው፡፡

‹‹አርአያ ባለ መሆን ነዋ› አልናቸው፡፡

Leave a Comment


four × = 12