ማንዴላ
ማንዴላ ማንዴላ ፤ ማንዴላ ማዲባ
አለቀስኩ ለኔ ፤ ውስጤ ላንተ አነባ
ለግል ሳይሆን ለሕዝብ ፤ ለቡድን ሳይሆን ለሀገር
በሞት መከራ እስር ፤ መቸም ጸንቶ መኖር
የኛ ጥቁር ዕንቁ ፤ የአፍሪካ ሞገሱ
መድኃኒቱ ነበርክ ፤ ለዘር መድሎ ምሱ
ብዙ ጥበብ አለህ ፤ ያንተ የማይረሱ
ለባለ እእምሮ ፤ ካንተ የሚወረሱ
ሊያውቀው የሚገባ ፤ ሁሉም ሰው እንደሱ
በተለይም መሪ ፤ የነከሰ ጥርሱ ፡፡
የማንዴላ ጥበብ ፤ የማንዴላ ትምህርት
ይቅር ማለት ከልብ ፤ ግን ደሞ አለመርሳት፡፡
ተቃርኖ ያላቸውን ፤ እንደ ውኃና ዘይት
ሁለቱን አዋሕደህ ፤ የኖርክበት ሕይዎት
ያስማማህበት ጥበብ ፤ ሁለቱን ባሕርያት
እጅግ ይገርመኛል ፤ የተካንከው ብስለት
የሚቻል የማይመስል ፤ እውን ሆኖ ማየት
በማንዴላ ልብ ውስጥ ፤ ተችሎ ዓየሁት
አዎ ይቅር እላለሁ ፤ ግን አልረሳም ላፍታ
ነበር ያልከው ያኔ ፤ ከእስር ስትፈታ ?
ውለታህን ሳስብ ፤ ላገሬ ያለህ ፍቅር
የእውነት ሰው መሆንህ ፤ ቃልክን የምታከብር
ሐዘን ይሰማኛል ፤ ዐይኔ እንባ በማቅረር፡፡
እንዲያ ሲያስጨንቀው ፤ ሲወርድ ሲወጣ
ኢትዮጵያን እንዳያይ ፤ ለሁለት ተቆርጣ
አንድነቷ እንዳይፈርስ ፤ እንዳትከስር ተሸጣ
ሲመክር ሲያባብል ፤ የሁለቱንም አውራ
እየተማጸነ ፤ አባብሎ እየጠራ
አንተ ጠቅላይ ሚንስትር ፤ አንተ ርእሰ ብሔር
ሆናቹህ አሥተዳድሩ ፤ ተሳስባቹህ በፍቅር
አንድ ሕዝብ የሆነውን ፤ አንድ ማንነት ስር
አታፈራቅቁት ፤ አትለዩት በድንበር
ተራርቆ የማይርቅ ፤ ተነጣጥሎ የማይቀር
ባለ አንድ መልኩን ፤ ያለውን ትስስር
ትዝብት አታትርፉ ፤ በቤተሰብ ፍቅር
ብዙ ነገር አለ ፤ የለም ተውት ይቅር
ለሀገር ጥቅም ሲባል ፤ የማትከፍሉት ነገር
መኖር የለበትም ፤ ምን ተአምር ቢፈጠር
ግድ የለም ባካቹህ ፤ መከፋፈሉ ይቅር
በእርጋታ እስኪ አስቡት ፤ ጠላት ወይስ ወዳጅ ?
ይሄ ነገር ቢሆን ፤ ሲቦርቅ የሚባጅ ?
አንድነት ነው ኃይላችን ፤ ጠላት የሚያሳፍር ፡፡
አላቸው ማንዴላ ፤ ከልምዱ ሲያስተምር
ያውቃልና ሴራው ፤ እንዳለው የማን ሸር
በጦቢያ ጥቅም ላይ ፤ ማን እንደሚቆምር ፡፡
ማዲባ ቀጠለ ፤ መለገሱን ምክር
ሁሉም ኃላፊ ነው ፤ አይምሰላቹህ የሚኖር
ለስማቹህ ኑሩ ፤ እሱ ነው የሚቀር
ታሪክ የሚያስበው ፤ ዘወትር የሚዘከር
ጥሩ በመሥራት ነው ፤ መከበር መፈቀር
ከመቃብር በላይ ፤ ዘለዓለም የሚኖር
ከጥፋት ምን አለ ? ከመጠላት በቀር ?
በራስ ሳይወሰን ፤ ቅስም የሚሰብር የዘር ፡፡
እድለኞች ናቹህ ፤ የዚች ታላቅ ሀገር
የሥልጣኔ ምንጭ ፤ ዋልታ ቋሚ ማገር
ተወላጆች ናቹህ ፤ ዜጎች የአርበኞች ዘር
ምድሯ ያበቀላቹህ ፤ ኢትዮጵያዊ ፍጡር
የተቀደሰ ሕዝብ ፤ የእግዚአብሔር ምድር
የጀግና ሕዝብ ፍሬ ፤ የአፍሪካ ክብር
እንደኔ እንደሌሎች ፤ በውርስ አይደለም
በፍቅሯ ተነድፈን ፤ የተጠመቅነው ስም
በሥጋ አጥንት ፍላጭ ፤ የወጣቹህ በደም ፡፡
ዓይታያቹህም ? ልዕልናው ክብሩ ?
አታውቁትም እንዴ ? ምን ነው አትፎክሩ ?
እኔ እንደማያቹህ ፤ በደም ወይ በትውልድ
ኢትዮጵያዊያን ናቹህ ፤ ባለ ዘንግ ባለ ዘውድ
ጣሊያን ወይ እንግሊዝ ፤ ዓረብ ወይም ሌላ
ምንም አትመስሉኝም ፤ ተልኮ ያለው ከኋላ
እንዲህ ሆኖ እያለ ፤ የማየው እውነታ
ለሀገራቹህ የማይበጅ ፤ ከእድገት የሚገታ
ኋላ የሚፈጥር ፤ ቁርሾና ቅሬታ
ለሰላም የማይበጅ ፤ የሚነሳ ፋታ
ሆድ የሚያሸካክር ፤ የእሳት ላይ ጨዋታ
አሁን የማታውቁት ፤ግን የማታ የማታ
የሚያመሰቃቅል ፤ በጊዜ ቆይታ
የምትመርጡበት ምክንያት ፤ አይገባኝምና
እንዳምን እገደዳለሁ ፤ ሲያቃዠኝ ነው ገና
ካልሆነ ግን እናንተ ፤ ጨርቅ ጥላቹሀል
ከሁለት አንደኛው ፤ በእርግጥ እውን ሆኗል ፡፡
የአሥተዳደር በደል ፤ ችግር አለ ተብሎ
ያንን በደል አድራሽ ፤ መጣል ነው እንጅ ታግሎ
የተገነባችውን ፤ ስንት ዋጋ ተከፍሎ
ልቁረስ አይባልም ፤ ሀገር ተገንጥሎ ፡፡
ማን አለባቹህ አሁን ? ያላቹህ እናንተ
ተቀናቃኝ የለ ፤ ከሄደ ሰነበተ
ተራው የእናንተ ነው ፤ ካለው እስከ ሞተ
በአንድነት በኅብረት ፤ መሥራት ነው በጋራ
በጥሩ አመራር ፤ እንደ ውኃ በጠራ ፡፡
እንደዚህ አርጉ እንጅ ፤ ስለ የደም ካሳ
ሀገር ጓሮ አይደለም ፤ የገበሬ ማሳ
ያም ያም ለብቻየ ፤ እያለ እያገሳ
የሚከፋፈሏት ፤ በእጣ ተቆራርሳ ፡፡
እንዲህ የሆነች ጊዜ ፤ ሀገር መሆኗ ቀርቶ
ብዙ ሽ መንደሮች ፤ ትሆናለች እንቶ ፈንቶ
ሀገር ሀገር የመሆን ፤ ዕድል የምታገኘው
አንተ ትብስ እኔ ፤ በሚል ተቻችለው
በአንድነት በኅብረት ፤ መኖር ስንችል ነው ፡፡
ነገር ግን ቅር ያለው ፤ ልቁረስ ባለ ቁጥር
መቆሚያው የቱ ላይ ፤ እንደሚሆን ድንበር
አስባቹህታል ? ምን እንደሚፈጠር ?
ታች መንደር ይወርዳል ፤ ጎሳንም ተሻግሮ
የየቡድኑ ቅልስ ፤ ትናንሽ የጅ ጓሮ
የሆነች ቁርስራሽ ፤ ልትሆን ነው ምንጣሮ ፡፡
እናም ሀገር ስንል ፤ ሕዝብ ብለን ስንጠራ
ስለ መገነጣጠል ፤ አንችል ልናወራ
አውራ ባለታሪክ ፤ የነጻነት ዘብ አጥር
የአንድነት ተምሳሌት ፤ ያጌጠ በኅብር
የአፓርታይድ ጠላት ፤ የቅኝ ግዛት ጸር
የጥቁር ሕዝብ ፈርጥ ፤ ኩራት ጌጥ ጋሻ ጦር
እንዴት ይሄን ያስባል ? እኮ በምን ተአምር ?
ካከበራቹህኝ ፤ ወንድም ነው ካላቹህ
ልመናዬን ስሙኝ ፤ ጆሮ ሰጥታቹህ
የምስራች ስጡኝ ፤ እሽ እንዳልክ ብላቹህ
እንቢ ካላቹህ ግን ፤ ቃሌን ካልሰማቹህ
ስሜን እንዳትጠሩ ፤ እኔም አልጠራቹህ ፡፡
አንድነት ወዳጣች ፤ ወደ ተቆረሰች
ከታሪኳ ጋራ ፤ ወደተካካደች
ከታላቅነቷ ፤ ወደተዋረደች
ድንቅ አርዓያነቷን ፤ ወርውራ ወደ ጣለች
እግሬን ላላነሣ ፤ ብየ ኢትዮጵያ አለች ፡፡
እለያቹሀለሁ ፤ በእግዚአብሔር ስም ምየ
ወንድም ሕዝብ ናፍቄ ፤ ላልመጣ ዐይኔ እያየ
ቤቴ እችለዋለሁ ፤ ራሴን አባብየ
ምንም ነገር ቢሆን ፤ እቆርጣለሁ ችየ ፡፡
ይሄ ሁሉ ምልጃ ፤ ያ ሁሉ ተማጽኖ
የኢሳይያስ መለስን ፤ ልብ አሳዝኖ
አርሞ ሊያቀና ፤ ሳይችል ቀረ መክኖ
የእነሱ ጭንቅላት ፤ ክፋትን ጠንጥኖ
ቆርጦ መቷልና ፤ ሊያጠፋ ጨክኖ ፡፡
የታላቁ ሰው ምክር ፤ የሚያነሣ አድኖ
ጭንጫ ላይ ተዘርቶ ፤ ውዱ ቃለ ፋኖ
በቅሎ ሳያፈራ ፤ ቀረ ከንቱ ባክኖ ፡፡
እነሱ የዕለቱን ፤ እሱ የሚያይ አርቆ
እነሱ ላይላዩን ፤ እሱ እጅግ ጠልቆ
እነሱ ያላዩትን ፤ ለእሱ የሚታይ ደምቆ
እሱ ይቅር ባይነት ፤ እነሱ መበቀል
እነሱ የጨለማ ፤ እሱ ደሞ የጸዳል
የሱ ጽናት ለእምነት ፤ የእነሱ ለክህደት
የእሱ አንደበት ለእውነት ፤ የእነሱ ለእብለት
እሱ እልፍ ነው ሲል ፤ እነሱ መቶ ዓመት
እሱ የኔም ነው ሲል ፤ የኢትዮጵያን እሴት
እነሱ የአንድ ዘር ነው ፤ መደምሰስ አለበት
እነሱ ጮርቃ እንጭጭ ፤ እሱ የበሰለ
የሰብእናን ጸጋ ፤ መንፈስ ባማከለ
እነሱ የደኸዩ ፤ እሱ የታደለ
እሱ አህጉራዊ ፤ እነሱ ጎጠኛ
እሱ የቸረ ለጋስ ፤ እነሱ ምቀኛ
እነሱ ጥላቻን ፤ እሱ ሰባኪ ፍቅር
እሱ የማቻቻል ፤ እነሱ የማቃቃር
እንደምን ይግባቡ ፤ ደናቁርት ከምሁር ?
ጦቢያም ተቆረሰች ፤ አካሏ ሁለት ሆነ
ማዲባ አለቀሰ ፤ አረረ በገነ
በኋላ ቆይቶ ፤ ብዙ ከሰነበተ
መለስ ባይገባውም ፤ እንደተሳሳተ
ማዲባን ሊፈትን ፤ እስኪ ይጸናል ቃሉ ?
አልመጣም እንዳለ ፤ ይቀራል ለበዓሉ ?
ብሎ ጥሪ አስላከ ፤ እንዲገኝ መጥቶ
ማንዴላ ሲሰማ ፤ አዘነ ተቆጥቶ
መጥቶም አልተገኘ ፤ ለጠሪው ክብር ሰጥቶ
ምንም እንኳን መርሑ ፤ ቢሆንም ይቅር ማለት
የኢትዮጵያ ነገር ግን ፤ የማይሆን ሆኖበት ፡፡
ማንዴላ ማንዴላ ፤ ማንዴላ ማዲባ
እንደተመኘላት ፤ አንድነት ለሳባ
ያችን ቀን ሲጠብቅ ፤ በደስታ ሊያነባ
እየፈነጠዘ ፤ ሊያድለን አበባ
አንድ ሆና ሳያያት ፤ ችግሯን አልባ
ሐዘን እንደበላው ፤ በሕልሙ እንደባባ
በእድሜ ተወስኖ ፤ ዐርፎ አፈር ገባ ፡፡
ኅዳር 2006 ዓ.ም.
ሠዓሊ አምሣሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Join Conversations