የወተት ጠብታ

Tebeta_Vl_by_biodome51የወተት ጠብታ

- 1 -

ቀዩ አቧራ ከእግሩ ስር ቡን እያለ ገዳዳ አምድ መስሎ ይነሳ ነበር፣አለማየሁ እየሮጠ ወደ እናቱ ሲሄድ።ከሰማያዊ ሸራ ጫማው አንስቶ አረንጓዴ ሱሪና ጃኬቱን እያለበሰ፣ልጩ ራሱ ላይ ጉች ያለች ቁንጮውን በጨረፍታ እየነካካ አቀብ ሲወጣ የአቧራው አምድ አባራሪ፣እሱ ተባራሪ ነበር የሚመስሉት።ለረፍት የተለቀቁ ተማሪዎች በጨርቅ ኳስ ሲራገጡ፣ ባልነካ እና ሌባና ፖሊስ እየተጫወቱ ሲሯሯጡ አለማየሁ ትንሽ፣ቀጭን ሰውነቱን እያጥመዘመዘ ተሽሎክልኮ ከአጥሩ ጥግ ጉብ ያለች ሳርማ መሬት ላይ ተቀምጠው ይጠብቁት እነበሩት እናቱ ጋር ደረሰ።

“ ቀስ ቀስ እመዬ እንዳትወድቅ! ” አሉት ክንፋቸውን ዘርግተው እየተቀበሉት።

አለማየሁ እየተንደረደረ ሄዶ ደረታቸው ላይ ተደፋ።ቀኝ እጁ ጡታቸውን ፍለጋ ተወነጨፈ።እናቱ ቁንጮውን በርህራሄ ደባብሰው ልጩ ራሱን ሳም አደረጉና ጡታቸውን አውጥተው ሰጡት።በሁለት እጆቹ ለቀም አድርጎ ሲምግ እሳቸው በቡድን ሆነው የሚመጡ ትናንሽ ልጆች ላይ አሻግረው አተኮሩ።

ከአለማየሁ በሁለትና በሶስት አመት ያህል ከፍ ከፍ የሚሉ አንድ አምስት ልጆች ይሆናሉ።ተለቅ ባለው ልጅ እየተመሩ ወደ እነ አለማየሁ ቀረቡ።በትናንሽ የህጻናት ፊቶቻቸው ላይ የደስታ ግርምት እየተነበበባቸው ግማሽ ክብ ሰርተው ቆሙና፣

“ እይዋቸው የአለማየሁን ላም! ” ብለው ተንጫጩ ።

አለማየሁ ጆሮ አልነበረውም።እናትዮው ግን ፈገግ አሉ።የልጆቹ አይኖች ልጃቸው አፍ ላይ እንዳያርፉ በነጠላቸው ሸፈን አደረጉትና፣

“ ልጆች እዚህ ምን ትሰራላችሁ? ሂዱ ተጫወቱ! ” አሉ የቁጣም የትዕግስትም ባልነበረ ድምጽ።

ልጆቹ አልሄዱም።በሳቅ እየተንጫጩ ፣

“ አለማየሁንና ላሙን ታያላችሁ?…አሌክስ ጡት ስትጠባ!ልክ እንደጥጃ!ውይ አሌክስ! ” ይሉ ጀመር፤አንዳቸው ላንዳቸው ተራ ሳይለቁ።

“እናንተም በየቤታችሁ ላሞች አሏችሁ ልጆች!በሉ አሁን ሂዱና ተጫወቱ!” አሉ እናት የመጣባቸውን ፈገግታ ጨቁነው ለመኮሳተር እየሞከሩ።

ልባቸው ውስጥ አንድ ደስ የሚል ስሜት ነበረበት፤የሌሎቹ ልጆች እናቶች ህጻኖቻቸውን ቸል ብለው በየቤታቸው ተቀምጠዋል።እሳቸው ግን ትምህርት ቤቱ ድረስ መጥተው ለመቁረጫ ልጃቸው ጡታቸውን ያጠባሉ፤አለኝታና መከታ ሆነውለታል።አንዳች የሚያህል ኩራት ልባቸው ውስጥ ሲገላበጥ ተሰማቸው።

“ አሌክስ እስቲ ከወተትሽ ለኛም አካፍይን!” አለ ከልጆቹ አንደኛው።

“ና ጥባ!ይበቃችኋል። ” አሉ እናት ወዳልተያዘው ጡታቸው እያመለከቱ።

የአለማየሁ እጅ ከመቅጽበት ተወርውሮ ጡታቸውን አፈነው።ተናጋሪው ልጅ መዳፉን አፉ ላይ አድርጎ እየተሽኮረመመ ሳቀ።

“ ና እንካ ጥባ ይበቃችኋል። ” አሉ ደገሙና ፈገግ ብለው።

አለማየሁ ጡቱን ይበልጥ አጥብቆ ሲይዝ ልጆቹ በደስታ ሳቅ ተንጫጩ።

“ ሂድ ጥባ አትፍራ! ” አሉት ጓደኞቹ ከኋላው እየገፋፉ።

“ አንተ ጥባ!አንተ ጥባ! ” እየተሳሳቁ ሲገፋፉ ሁለቱ አለማየሁ እናት እግር ስር ወደቁ።ደረታቸው ላይ ተለጥፎ በአፉ አንዱን፣በእጁ ሌላውን ጡታቸውን የጨመደደው ልጃቸው አላላውስ አላቸው እንጂ የወደቁትን ልጆች ሊያነሷቸው ቃጥቷቸው ነበር።ልጆቹ ግን አንሺም አላስፈለጋቸው፤ተነሱና አቧራቸውን እንኳ ሳያራግፉ እነሱም በተራቸው ሌሎቹን ሊጥሉ ልፊያ ያዙ።

እናት የልጅነትን ሳቂታነትና ብሩህነት በአካላዊ አይኖቻቸው እየተመለከቱ፣በአይነ-ህሊናቸው ደግሞ የሩቅ ጊዜ እሷነታቸውን አስተዋሉ።እሳቸውም አንዴ፣ያን ጊዜ እንዲህ አይነት የግዴለሽነት ዘመን አሳልፈዋል።ሽውታው ሽው አላቸው።በገጽታቸው ላይ የሚጫወተው ህልማዊ ፈገግታ ቀይዳማ እናታዊ ፊታቸውን ወደ ልጅነት የለወጠው ይመስል ነበር።

ሕጻናቱ እየተንጫጩና እየተሳሳቁ አፍጥጠውባቸው፣አለማየሁም የእናቱን ጡት እየመገመገ፣እናት በልጆቹ በኩል የራሳቸውን ልጅነት እየኖሩ አስራ አምስቷ ደቂቃ ተጠናቀቀች።ደወሉ ሲደወል ልጆቹ ብር እያሉ ወደ መጡበት ሲመለሱ፣

“ አሌክስ ጡትሽን ትተሽ ብትማሪ ይሻልሻል!” አለ አንዱ።

አለማየሁ ቀናም አላለ።ይህን አስቀያሚ ድምጽ ያለውን ደወል ጥልት አደረገው።ለሱ ይህ ደወል የተለየ መልክ ነበረው፣አስቀያሚና ውብ።በእረፍትና ወደቤት መሄጃ ሰዓት ሲደርስ የሚኖረውን ውብ ቃና ያህል ወደ ክፍል መግቢያ ሰዓት ላይ ሲደወል የሚያስጠላ ቃና ይኖረዋል።

“ በል ተነስ አለማየሁ…ተነስና ወደ ክፍል ግባ! ” አሉት እናት።

ለልጃቸው ሆዳቸው ባብቷል።ልጃቸው ከጡቱ ተነጥሎ ወደማይፈቅደው ክፍል መግባቱ ልባቸውን ይንካው እንጂ ስሜታቸው መገለጽ የለበትም።አለማየሁ ቀና ብሎ በለማኝ አይኖቹ ተመለከታቸው።

“ አይዞህ የኔ ጌታ!ሂድ ግባ።እኔ እዚሁ ሆኜ እጠብቅሃለሁ፣እሺ የኔ ጎበዝ ተማሪ? ”

“ አንቺ የትም አትሄጂ ? እዚሁ ትሆኛለሽ? ” አለ ባርባር እያለው።

“ እዚሁ እጠብቅሃለሁ የኔ ቆንጆ፣አሁን ግባና ተማር። ”

“ ክፍል ድረስ አድርሺኝ!”

ጡታቸውን ወደ ደረታቸው መልሰው ነጠላቸውን አጣፉና እጁን ይዘውት ወደክፍሉ አመሩ።

“ ግን እስከሚደወል ድረስ አትሄጂም አይደለ?” አለ ቀና ብሎ።

“ አልሄድም የኔ ቆንጆ። ”

“ የት ሆነሽ ነው የምትጠብቂኝ? ”

“ እዚያው አሁን የነበርንበት ቦታ! ”

አለማየሁ በመጠኑ ቀለል ቢለውም ወደ ክፍል በቀረበ ቁጥር ግን ርምጃው ሲጎተት ይታይ ነበር።አሁን ተማሪዎች ሁሉ በየክፍላቸው ገብተው ሜዳው ጭር ማለት ጀምሯል።አቧራማው ሜዳ ላይ የወዳደቁትን ቁርጥራጭ ወረቀቶች ነፋሱ እያንሻተተ ይገፋፋቸዋል።አጥሩ ጥግ ከበቀሉት ዛፎች ላይ አንዳንድ ወፎች ሲንጫጩ ይሰማል።ክፍሉ ለመድረስ አንድ ሁለት እርምጃ ሲቀራቸው አለማየሁ እንደገና ቀና ብሎ እንባ ባቆረዘዙ አይኖቹ እያያቸው፣

“ እማ ጥለሽኝ እንዳትሄጂ ግን ጠብቂኝ! ” አላቸው።

እናት በአይናቸው ብቻ ቃል ሲገቡለት ልባቸው ግን ልባቸውን ታዘበው። የልጃቸውን ትንሽ መዳፍ ጨብጠው የመጎተት ያህል ወደ ክፍል ሲያስገቡት ጓደኞቹ፣ “ የአሌክስ ላም!” ብለው አንዴ ተንጫጩ ።ክፍሉ በሳቅ አውካካ።

ከውካታው በላይ ድምጻቸውን ለማሰማት ጮክ ብለው “ አለቃው ማነው? ” ሲሉ ጠየቁ እናት በቁጣ ተኮሳትረው።

ድንገት ጸጥ ረጭ ባለው ክፍል ውስጥ “ እኔ ነኝ!” አለ እየተጠራጠረ፣ ከተማሪዎቹ ሁሉ ጎላ ብሎ የሚታይ ልጅ።ከመቀመጫው ተነስቶ በዝግታ ወደ እናት ሲሄድ የሚባባሉትን ለመስማት ተማሪዎቹ ጆሮዎቻቸውን አቆሙ።

“ ጎሽ የኔ ልጅ ወንድምህን ጠብቀው እንዳያለቅስ!” እያሉ የአለማየሁን እጅ ለአለቃው አስረከቡት “ እኔ ውጪ እጠብቀዋለሁ። ”

“ እሺ እርስዎ መሄድ ይችላሉ እማማ!እኔ እጠብቀዋለሁ።”

እናት አቆልቁለው የልጃቸውን አይኖች ተመለከቱ።የተቃውሞ እንባ አቆርዝዘዋል።

“ የለም አንተ እዚሁ ክፍል ውስጥ ጠብቅልኝ።እኔ ውጪ እቆየዋለሁ።” የታችኛውን ከንፈራቸውን ነከስ በማድረግ አለቅዮውን ጠቀሱት።

“ እሺ እማማ! ” አለቃው አለማየሁን ይዞ ወደ መቀመጫው መራው።

እንደተቀመጠ ለመጨረሻ ጊዜ እናቱን እየተቁለጨለጨ አያቸው።

“ እዚሁ እቆይሃለሁ!ጎሽ የኔ ተማሪ፣ አይዞህ! ” ብለውት ሲወጡ ከመምህሩ ጋር ፊት ለፊት ተጋጠሙ።

***
ከአንድ ወር በፊት መሆኑ ነው።መስከረም ጠብቶ፣አደይ አበቦች ፈክተው የየመንገዱን ዳር ዳር ቢጫ መቀነት አልብሰውት ነበር።የጨቀየው መሬት ጠፈፍ ብሎ፣በየጎዳናው ላይና በየጥጋጥጉ ጉድጓድ ሰርቶ ያቆረው ውሃ ተንኖ፣ነገር ግን ምድር ገና በአረንጓዴ ርጥበት እንደተነከረች ነበረች።ተማሪዎች ቦርሳዎቻቸውን አንግበው ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ተዘጋጅተው፣ከሁለት ወራት ረጅም ረፍት በኋላ አዳዲስ ልብሶቻቸውን ለብሰው ከየጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ናፍቀዋል።ህይወት ሳቅ ፈገግ ብላ የተለምዶ ኑሮዋን ለመቀጠል ቸኩላለች።

እና የአለማየሁ እናትም አዲሱን አመት በአዲስ ድል ለመቀበል ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው መነሳታቸውን ቤተሰቡ ሁሉ አውቆታል።ኑሮ ከጊዜ ወደጊዜ ከበድ እያለ መጥቷልና በአዲስና ጠንካራ ጉልበት መያዝ ይገባዋል።አራቱን ልጆቻቸውን ከንግድ ት/ቤት አስወጥተው መንግስት ት/ቤት ከጨመሩ አመታት አልፈዋል።አሁን የቀሩት ሁለቱ የመጨረሻ ልጆቻቸው ብቻ ነበሩ።ታላቅየው አፈወርቅ አምስት አመት ከመንፈቁ ሲሆን ታናሹ አለማየሁ ገና የአራት አመት ህጻን ነበር።አፈወርቅ ቄስ ት/ቤት ለስድስት ወራት በመቆየቱ ማንበብና መጻፍ ሲችል አለማየሁ ግን ገና የፊደልን ዘር እንኳ አያውቅም።

ሁለቱን ወንድማማቾች ግራና ቀኝ ይዘው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው የመንግስት ት/ቤት ሲሄዱ የቀደሟቸው ጥቂት ነበሩ።የት/ቤቱ ባልደረቦች እስኪመጡ ድረስ ግን ወላጆችና ልጆቻቸው የት/ቤቱን መግቢያ አጣበቡት።አዳፋ ነጫጭ ሸማዎች፣እዚህና እዚያ የተቀዳደዱ የፈረንጅ ቀሚሶች፣ከተረከዛቸው የተተረተሩ ኮንጎ ጫማዎች ያጠለቁ እናቶች፤የተጣጣፉ ካኪ ሱሪና ቁምጣዎች፣ከጉልበታቸውና ከቂጣቸው የተቦተረፉ ቦላሌዎች፣ትከሻቸው ላይ የተተረተሩ ሹራቦች፣አውራ ጣት ብቅ ያደረጉ ሸራ ጫማዎች ካለበሷቸው ልጆቻቸው ጋር።ፀአዳ ልብሶች ለብሰው ልጆቻቸውን እንደነገሩ ያለበሱ ወላጆች።እነሱም ልጆቻቸውም ፅዱ የለበሱ ወላጆች።ይህ ሁሉ ህዝብ ወገን ሳይለይ ተሰበጣጥሮ ቆሞ ቡራቡሬ ሰብአዊ መንጋ ፈጥሯል።ከዚህ ሁሉ ህዝበ-መዓት መካከል ለልጆቻቸው የመንግስት ት/ቤት አገኛለሁ ማለት የህልም ያህል ርቆ ቢታያቸውም ህልም እውን የማይሆንበት ምክንያት የለም፤ጥረት ከታከለበት አላቸው የህሊናቸው ግማሽ።

ቅጥር ግቢው ውስጥ ከጠረጴዛ ኋላ ተቀምጠው የት/ቤቱ ባለስልጣኖች አዲስ ገቢዎችን መመዝገብ ጀመሩ።በር ላይ ትንቅንቁ፣ጉሽሚያውና ስድቡ አይጣል ነው።ዘበኞች አንዴ በጉልበት፣አንዴ በማግባባት ስርአት ለማስጠበቅ ይጥራሉ።መዝጋቢዎች ስርአት ካልተጠበቀ እንደማይመዘግቡ ይዝታሉ።ልጆቻቸውን ወደጥግ አስቀምጠው እናት ትንቅንቁ ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል።ቀድሞ የመጣ ቀድሞ ይስተናገዳል የሚል ህግ ባልነበረበት በዚህ ቦታ ፊትም ሆነ ኋላ መምጣት ዋጋ አልነበረውም።በገፉ ጊዜ ወደፊት ሲሉ፣በተገፈተሩ ወቅት ደግሞ ወደኋላ ሲመለሱ ሁለት ሰዓቶች አለፉ።ቀይ ዳማ ፊታቸው አመድ መስሎ በስጋት ይጠብቋቸው ወደነበሩት ግልገሎቻቸው ተመልሰው ጥውልግልግ ያሉትን ችግኞች ግራና ቀኝ አንጠለጠሉና ባቅራቢያ ወደነበረ ሻይቤት ገቡ።ለልጆቹ ሻይና ፓስቲ ገዝተው አብልተው፣እሳቸውም ሁለት ብርጭቆ ውሃ ግጥም አድርገው ጠጥተው ወደ ትግሉ ሜዳ ሲገቡ ሰዓቱ ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ሆኖ ነበር።

ውጤት አልነበረውም።ቀስ በቀስ ፀአዳ ልብስ ለባሾቹ ወላጆች እና ከእድፋሞቹም ጥቂቶቹ ስልችት ብሏቸውና ደክመው ከትግሉ ሜዳ ማፈግፈግ ጀመሩ።ጊዜው ገና ድሮ እኩለቀን ሆኗል።መዝጋቢዎቹም ደክሟቸዋል።የምሳ ሰዓት ነው።ወደቤት ከመመለስ ሌላ አማራጭ አልነበረም።

ይህን መሳይ ትንቅንቅ ለሁለት ቀናት ቀጠለ።በሶስተኛው ቀን እናት ድል አደረጉ።መጀመሪያ መዝጋቢዎቹ ጋር እንደቀረቡ ያስመዘገቡት አፈወርቅን ነው።መዝጋቢው ከእግር እስከራሱ አየውና፣

“ ስንት አመቱ ነው? ” ሲል ጠየቀ።

ያፈወርቅ ብስል ቀይ ፊት ቲማቲም መስሎ፣ረጅም የሉጫ ጸጉር ቁንጮው ግንባሩ ላይ ዘፍ እንዳለ እናቱንና መዝጋቢውን በየተራ ይመለከታል።

“ እንግዲህ አምስተኛውን ማገባደዱ ነው። ” አሉት።

“ እውነተኛ እድሜውን ነው የጠየኩዎት። ”

“ እውነተኛውን ነው የነገርኩዎት ጌታዬ!አምስት አመት ከመንፈቅ። ”

“ ታዲያ ገና ልጅ ነዋ! ”

“ ለትምህርት ልጅ አይደለም ጌታዬ! ሁለቴ ዳዊት ደግሟል!ማንበብና መጻፍም አሳምሮ ይችላል።” ድምጻቸው ለማኝም፣ደፋርም፣ቁጡም ነበር።

ተመዘገበ፤አፈወርቅ ለማ።ይህ የሆነው ጧት ሶስት ሰዓት ላይ ነበር።እናት በዚህ ብቻ አልረኩም።አለማየሁ ለማም መመዝገብ አለበት።ከዚያ ሁለቱም ችግኞች እንደምስጉን ተማሪዎቹ ታላላቆቻቸው የመንግስት ተማሪዎች ይሆናሉ።

እዚያው ዋሉ።ቀትር ላይ መዝጋቢዎች ከተቀመጡበት ተነስተው ወደቢሮ ሲገቡ እድል ያልቀናቸው ወላጆች ተስፋ ቆርጠው ወደየቤታቸው መበታተን ጀመሩ።እናት የተዘናጋው ዘበኛ ሳያያቸው በፊት ትንሹን ልጃቸውን አፈፍ አድርገው በበሩ ዘው! ዘበኛው ምን እንደተሰራ ሲገነዘብ እሳቸው መዝጋቢው ቢሮ ገብተዋል።ከቀኑ አሰልቺ ስራ በኋላ እፎይ ብሎ ምሳውን ለመብላት የቋመጠው መዝጋቢ ወረቀቶቹን በቁሙ ጠረጴዛው ላይ ጥሎ ለመውጣት ሲዘጋጅ ነበር የደረሱበት።

“ ምን ይፈልጋሉ? አሁን ምሳ ሰዓት ነው።ከሰዓት ይመለሱ!” በአንድ ትንፋሽ።

“ ጌታዬ አንዴ ይስሙኝ!ካሉት ልጆቼ ሁሉ ይህ ብቻ ነው ት/ቤት ሳይገባ የቀረብኝ።እባክዎ የወንድሞቹ ወግ ለሱም ይድረሰው! ”

“ አሁን ለምሳ መውጣቴ ነው በኋላ ይመለሱ አልኩኝ እኮ! ”

“ ስመላለስ ሳምንት ሆኖኛል ጌታዬ!እባክዎ ይርዱኝ! ”

የስልቹነት ገለጻ ጥቁር አራት መዓዘን ፊቱን እያጠለመው “ ነገርኮት እኮ!” እንዳለ ወዲያው ድንገተኛ ትውስታ ስልቹነቱን እየተካው “ ከዚህ በፊት አላስመዘገቡም እንዴ? ” አላቸው።

እናት ለመዋሸት ከጅሏቸው ከህሊናቸው ጋር ለቅጽበት ታገሉ። አለማየሁ ፈርቶ በእናቱ ቀሚስ ግማሽ ፊቱን ሸፍኖ ተሸጉጧል።

“ ታላቅየውን ነው ጌታዬ!” አሉ እናት በመጨረሻ።

“አለመኛ ነዎት!ሌላው ለአንድ ልጅ አጥቷል እርስዎ ሁለት ልጆች ላስመዝግብ ይላሉ?!”

ወደ ውጪ ለመውጣት ነቅነቅ አለ።

“ ሁሉም የልፋቱን ያግኝ ጌታዬ! እንደልፋቴማ ቢሆን እንኳን ሁለት አራት ልጆችም ቢመዘገቡልኝ አይበዛብኝም!”

ሰውዬው በመገገረም ገላመጣቸውና ወደበሩ እመር ሲል፣ እናት እግሩ ላይ ሲደፉና የደነገጠው አለማየሁ እሪ ሲል አንድ ሆነ።መዝጋቢው ያጎነበሱትን እናት ጀርባና ተሸብሮ የሚንጫረረውን ህጻን በተገርሞ ቁልቁል እየተመለከተ ሳይታወቀው ጠምዘዝ ብሎ ከጠረጴዛው ላይ የመመዝገቢያ ወረቀቱን አነሳ።

ዘበኛው ይሄኔ ነበር የመጣው።የምክትል ዲሬክተሩን እግር ጨምድደው ቁጢጥ ያሉትን እናትና በሲቃ የታፈነ ልጃቸውን ሲያይ በገጽታው ላይ የነበረው አስፈሪ ገለጻ እንደጢስ በኖ ጠፋ።ወደ ቢሮው ውስጥ ገብቶ አለቃውን “ምን ልርዳህ ጌታዬ? ” ከማለት ግን አልተቆጠበም።

“ የምትረዳኝማ በሩን በደንብ በመጠበቅ ነበር!” ደም በሚተፉ አይኖቹ ዘበኛው ላይ አፈጠጠበትና ወደ እናት መለስ ብሎ “ ስንት አይነት ችኮ ሰው አለ እባካችሁ? ለመሆኑ ስንት አመቱ ነው ?! ይነሱና ይንገሩኝ! ” አለ በስልቹነት።

እናት ትንሽ እንደማወላወል ብለው “ አራት አመቱ ነው ጌታዬ!” ሲሉ መለሱ።

የንዴት ሳቅ ሳቀና ሰውየው “ ጡት ያልጠገበ ልጅ አምጥተው ታዲያ ምን አድርግ ይሉኛል? ”

“ ይመዝገብልኝ እንጂ ጡትስ አጠግበዋለሁ! ” አሉ እናት ቀና ሳይሉ።

“ አንድ አመት ጡት ያጥግቡትና ይመለሱ! ”

“ እየተማረ ጡት አጠግበዋለሁ። ” ችክ አሉ።

ለረጅም ደቂቃ ቁልቁል ተመለከታቸው፤ጥቁር ፊቱ በርህራሄም፣በስልቹነትም፣በብስጭትም

፣በአግርሞትም ተዝጎርጉሮ።

“ ስሙ ማን ይባላል? ”

“ አለማየሁ ለማ!የልጆችዎ አባት ያድርግዎት ጌታዬ!”

***

ደግነትን ራሱን በሆነው በእናቱ ገጽታ ፈንታ የተመለከተው ኮስታራውን የመምህሩን ገጽታ ነበር፣አለማየሁ እናቱ ወደ ወጡበት ክፍል መምህሩ ሲገቡ።በትናንሽ ቀያይ አይኖቻቸው ተማሪዎቹን ከዳር ዳር ቃኝተው ሲያበቁ አለቃው ጥቁሩን ሰሌዳ እንዲያጸዳ አዘዙ።

አስተማሪው እሱን ነጥለው አይተው፣እሱን ብቻ የሚያናግሩት ወይም የልቡን አውቀው የሚቆጡት እየመሰለው ትንሽ ሰውነቱ ተኮመታትራ ይበልጥ አነሰች።ትናንሽ አይኖቹ ያረገዙትን እንባ ጠብ ጠብ ሲያደርጉ ወደ ዴስኩ አቀርቅሮ እናቱ ያስቀመጡለትን መሀረብ ከጃኬት ኪሱ ውስጥ አወጣና አይኖቹን ጠራረገ።

“ ተማሪዎች የዛሬ ትምህርታችን…” የአስተማሪው ጎርናና ድምጽ ክፍሊቱን ሞላት።

አለማየሁ የተቀረውን አልሰማም።ልቡ ከክፍል ውጪ ነበረች፤አጥሩ ጥግ፣ምቾት ፍቅርና ደስታ የምትሰጥ ውብ ፍጡር ካለችበት በሳር የተሸፈነች ቁራጭ መሬት ላይ።ክፍለ-ጊዜው የክፉ ቀንን ያህል ረዘመበት።ክፍሊቱን ጥልት አደረጋት።በራሪ ልቡንና ትንሽ ሰውነቱን ጠፍራ ያሰረች ጠፍር፣እፍን አድርጋ የያዘች እስር ቤት መስላ ታየችው።

እፎይታ የተሰማው የክፍለ-ጊዜውን ማብቃት የሚያበስረው ደወል ሲንጫረር ነበር።በደመ-ነፍስ እርሳስና እስኪሪፕቶውን ኪሱ ውስጥ ሸጎጠና የመምህሩን እግር ተከትሎ ወደውጪ ሊፈተለክ ሲል አንድ ጠንካራ እጅ የጃኬቱን አንገትጌ ጨመደደው።

“ ወዴት ነው ክፍልህን ትተህ የምትሄደው? ” አለቅየው።

“ ሽንቴ መጥቶብኝ ነው! ” እንባው አንዴ ችፍ አለ።

“ በኋላ ትሄዳለህ!አሁን ቁጭ በል! ”

“ ልቀቀኝ ሽንት ቤት እሄዳለሁ! ” ድምጹ በለቅሶ ታጅቧል።

“ እባክህ ላሟ ጋር መሄድ ፈልጋ ነው። ” አንድ አሿፊ ድምጽ።

አለማየሁ ከምር አለቀሰ።

“ እባክህ ልቀቀውና ሸንቶ ይመለስ!” ያዘነ የሴት ድምጽ።

“ ውይ ሲያሳዝን! ” ሌላ የሴት ልጅ ድምጽ።

“ ወተትዋን ላስ ላስ አድርጋ ትምጣ እባክህ ልቀቃት። ”

“ አይ አሌክስ ቁንጯሟ! ”

“ እሺ ቶሎ ትመለሳለህ? ”

“ እ? አዎ!” አይኑን እያሻሸ።

የጃኬቱ አንገትጌ ሲለቀቅ ከአንዳች ቀፋፊ ነገር ጭብጥ ውስጥ የወጣ ያህል ነበር የተሰማው።ከክፍል ብር ብሎ እንደወጣ አይኖቹን ወደ ሳርማዋ የአጥር ጥግ ወረወረ።ጭር ባለው ግቢ ውስጥ ጭር ብላለች።ቅድም እናቱ የነበሩባት ቦታ አሁን ባዶ ሆና ከበስተኋላዋ የበቀለችው ለጋ ባህርዛፍ በነፋስ ሃይል ጎንበስ ቀና ስትል በእናቱ ምትክ ልታስተናግደው ‘ና ወዲህ!’ የምትለው መሰለው።ግን አላመናትም።መጥፈፍ የጀመረው እንባው እንደገና ገነፈለ።ወደዚያ ወደሚጠላውና ደግነት ወደጎደለው ክፍል ዳግመኛ ሊገባ አልፈለገም።የግዴለሽነት ቅዝቃዜ ሰውነቱን የሚያኮማትረው ነበር መስሎ የሚሰማው።

እንዲያው ብቻ ብር እያለ ቀዩን አቧራ አቋርጦ ወደ በሩ ገሰገሰ።መሀል መንገድ ላይ እንደደረሰ የደብተሩ አለመኖር ታወሰው።እርሳሱና እስኪሪፕቶው ጃኬት ኪሱ ውስጥ ተገትረዋል።ስለደብተሮቹ አልተጨነቀም።ይልቅስ ያስጨነቀው ፊትለፊቱ የሚንጎማለለው ዘበኛ እና ወደ ቤቱ መሄጃ ሰበብ አለማግኘቱ ነበር።እንደዋዛ ጥሩ ሰበብ ተገለጸለት።

እርሳስና እስኪፕቶው ቢጠፉ በነሱ ሰበብ ወደቤት መሄድ ይችላል።አይኑ እያየ ግን ሊጥላቸው አልደፈረም።የጃኬቱን ኪስ በእስክሪፕቶው ወግቶ ተረተረና መፃፊያዎቹን በቀዳዳው ትይዩ ኪሱ ውስጥ ገተራቸው።የጎማ ቱቦ ይዞ የሚንጎማለለው ዘበኛ ድንገት ቢያየው የሚያርፍበት አለንጋ ሳይነካው ቆጠቆጠው።እንዴት ይሸውደው?የሜዳው ጭርታ ያስፈራራል።እሱ ብቻውን አረንጓዴ ጃኬትና ሱሪውን እንደለበሰ፣በቀዩ አፈር ላይ የበቀለ ብቸኛ ችግኝ ይመስላል።ወደ አጥሩ ተራምዶ ጥግ ጥጉን ከተተከሉት ለጋ ዛፎች ጀርባ እየታከከ ወደበሩ ተጠጋ።ዘበኛው መንጎራደዱ ሲሰለቸው ወደ ጥበቃ ቤቱ ይገባና ተመልሶ ይወጣል።አለማየሁ ትንፋሹን ቆርጦ፣ አይኖቹን አፍጥጦ በንቃት ይከታተለው ጀመር።አሁን ዘበኛው ወደአለማየሁ አቅጣጫ ፊቱን መለሰ።አለማየሁ ባለበት እንደውሃ ፈሰሰ።ወዲያው ዘበኛው ሁለት እርምጃ ወደፊት ተራመደና ተመልሶ ወደዘበኛ ቤቱ ውስጥ ጥልቅ ሲል ወደ አይኖቹ የመጣው እንባ መለስ ብሎለት ትንሹ ሚዳቋ ሚጢጢ ልቡ አረፍ ስትል ተሰማው።በዚህ አይነት ሙሉ ሩብ ሰዓት አለፈ።

ትንሽ እጁን ወደጃኬት ኪሱ ሰደደ።ጣቶቹ ዘለው የገቡት እስክሪፕቶው የፈጠረው ትርትር ውስጥ ነበር።እርሳስ የለም።እስክሪፕቶም አልነበረም።አለማየሁ ወደኋላው ዞሮ መመልከት አልፈለገም።ልቡና እሱ ተዋውቀዋል።እፎይታ ተሰማው።

የት/ቤቱ ርዕሰ-መምህር በቢሮው መስኮት በኩል ዘበኛውን ጠርቶ አንገቱን መልሶ ሲያስገባ ከሩቁ በተመለከተ ጊዜ አለማየሁ ልቡ በሺህ የተለያዩ ሃሳቦች ተወጥራ ነበር።ዘበኛው ወደ ርዕሰ-መምህሩ ቢሮ ሲሔድ በደስታና በጉጉት ሲቃ ታንቆ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደማያገኝ የተረዳው ትንሽ አረንጓዴ ሚዳቋ ከተደበቀበት ጥግ ቱር ብሎ ወደ በሩ ፈረጠጠ።

መኖሪያ ቤቱ ሩቅ አልነበረም፡፡ ግቢ ውስጥ ከች ሲል እናቱ በድንጋጤ ክው ብለው ቀሩ።

“ ምነው የኔ ጌታ ምን ሆንክ? ” ብለው ጠየቁት።

“ ምንም አልሆንኩ! ”

“ ምነው ቶሎ ተለቀቃችሁ? ደብተርህስ የታለ? ”

“ እዚያው ነው የተውኩት፣ት/ቤት! ”

“ ለምን? ”

“ ገና አልተለቀቅንም እኮ! ”

“ ታዲያ ለምን መጣህ? ”

“ እርሳስና እስክሪፕቶ ጠፍቶብኝ። ”

“ የት ጣልከው? ”

“ እኔ እንጃ! በዚህ ቀዳዳ በኩል ነው የጠፋብኝ ”

የተተረተረውን የጃኬቱን ኪስ አሳያቸው ።

-2-

“… ባልተጠናና ባልታቀደ መንገድ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋምቤላና መተከል እንዲዘምቱ መደረጉ በቁጭት የምናስታውሰው የቅርብ ዚዜ ትዝታ ነው…” ከተናጋሪው ንግግር ሁሉ ይህኛው ህሊናውን ሰርስሮት ገባ፤አለማየሁን።

መድረኩ ላይ ካለው ጠረጴዛ ጀርባ የኢትዮጵያ ባንዲራ ግርግዳውን በከፊል አስጊጦታል።ከጠረጴዛው ኋላ ካሉት ወንበሮች ላይ ጥቋቁር ካባዎች ከጥቋቁር ቆቦች ጋር ያደረጉ የዩኒቨርሲቲ ባለስልጣኖች ተኮልኩለው፣እንደነሱው ጥቋቁር ካባና ቆብ የተጎናጸፉ ተማሪዎችና በተለያዩ አልባሳት የደመቁ ወላጅ ዘመዶቻቸው የመሉትን አዳራሽ ቁልቁል ይመለከታሉ።ከሁለት አመታት አንስቶ እስከ ስድስት አመታት የሚፈጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው በማገባደድ ለወግ ለማዕረግ የደረሱ ዕጩ ምሩቃንና ምሩቃን የተገጠገጡበት አዳራሽ በደስታና በዕርካታ ተሞልቷል።

የአለማየሁ ታላቅ ወንድም፣የመጀመሪያው ማለት ነው፣ከስምንት አመት በፊት በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ነበር።መተከልና ጋምቤላ በተዘመተበት ወቅት እሱ የሶስተኛ አመት ተማሪ ነበር።በህመም ሳቢያ በዘመቻው ላይ ባለመሳተፉ እንዳይማር ካገዱት ሰዎች አንዱ እኚሁ ያሁኑ ተናጋሪ ነበሩ።አለማየሁ አንጋፋው ወንድሙ የነገረው ትዝ አለው…

*

የተንጣለለውን መተላለፊያ አቋርጦ ወደ ፀሀፊያቸው ቢሮ ሊገባ ሲል እሳቸው ከቢሯቸው በግል በራቸው ሲወጡ ተገናኙ።

“ ቀጠሮ አለህ? ” ነበር ያሉት መለስ ብለው።

“ ቀጠሮ አልያዝኩም!እ…ግን ባለፈው ዘመቻ በህመም ምክንያት ባለመሳተፌ ሪ ሬጂስትሬሽን አልፎኛል።የሃኪም ማስረጃ ስላለኝ እንድመዘገብና ትምህርቴን እንድቀጥል እንዲፈቀድልኝ ላመለክት ነበር የመጣሁት። ” አላቸው።

ወደውጪ ለመውጣት መንገድ ጀምረዋል።ከጎን ለጠቃቸው።

“ ታዲያ አሁን የሃኪሞች ቦርድ ወረቀት አለኝ ነው የምትለው? ”

“ የቦርድ ወረቀት ሳይሆን የታከምኩበት ማስረጃ ነው ያለኝ። ”

“ እሱ አይሆንም! ” ጨለም ያለውን አዳራሽ አልፈው የፀሀይ ብርሃን ወዳጥለቀለቀው መግቢያ ወጡ።መኪናቸው በስተግራ ቆማ ነበር።ወደዚያው እያመሩ “ የቦርድ ወረቀት ከአለህ ደህና!አለበለዚያ ግን የሃኪም ማስረጃ ብቻ አይበቃም። ” አሉት ደገሙና።

መኪናቸው ውስጥ ሲገቡ እሱ እንደቆመ እንባውን እየታገለ “ እባክዎት…” ከማለቱ የመኪናዋ ሞተር ተነሳ።ወደኋላ ስትንቀሳቀስ እሱም ወደኋላ፣ወደፊት ስትሽከረከር እሱም ወደፊት…ወዲያው ተስፈንጥራ ስትጠመዘዝ የሚያፈገፍግ ቂጧን እንባ ባረገዙ አይኖቹ ተከተላት።ወደቤቱ መሄድ አልፈለገም።ምን ተይዞ ጉዞ!ፊቱን መልሶ ወደአዳራሹ ገባ።ፀሀፊዋን ቀጠሮ አስይዞ ሲወጣ ልቡ በገሚስ ተስፋ ተሞልታ ነበር።

በቀጠሮው እለት ወደ ባለስልጣኑ ቢሮ ሲገባ የተመለከተው ከፀሀፊዋ አዳራሽ በእጅጉ ያነሰ ክፍል ነበር።በትህትና ተቀብለው ወንበር ላይ እንዲቀመጥ አመለከቱት።

“ ምን ነበር ችግርህ? ”

“ ትላንትና እንደነገርኮት ታምሜ ሆስፒታል ገብቼ ስለነበር በዘመቻ ላይ ልሳተፍ አልቻልኩም።የሃኪም ማስረጃ አለኝ።ስለዚህ እንደገና ልመዝገብና ትምህርቴን እንድቀጥል ይፈቀድልኝ። ”

“ በመጀመሪያ ደረጃ ሪ ሬጂስትሬሽን ያስፈለገው እንዳንተ ያሉትን ለመያዝ ነው።በሁለተኛ ደረጃ በዚህ ዘመቻ ላይ እኛ ብቻ ሳንሆን የመንግስት ባለስልጣናትም የተሳተፉበት በመሆኑ እኔ ምንም ልረዳህ አልችልም!አልፈልግምም! እንደማንኛውም ተማሪ መዝመት ነበረብህ፣ግዴታህም ነበር! ”

“ ህመም ተፈጥሯዊ ነው፣ቀጠሮም አይሰጥም! እና በህመም ሳቢያ መዝመት ካልቻልኩ መማር የለብኝም? ”

“ የሃኪሞች ቦርድ ወረቀት ማቅረብ ከቻልክ ብቻ! ”

“በርስዎስ በኩል ትምህርቴን እንድቀጥል ሊረዱኝ አይችሉም? ”

“ አልችልም! አልፈልግምም! ”

ተሰናብቶ ወጣ።

እና አንድ አመት አቃጠለ።

ቆይቶ ነበር የተመረቀው።

*
አለማየሁ ከሄደበት የትውስታ አለም ወዳለበት አዳራሽ በገጭታ ተመለሰ።ሰውዬው ንግግራቸውን ሲጨርሱ አዳራሹ በጭብጨባ ሸኛቸው።አለማየሁ የቆቡን መነሳንስ በዝንጋታ እየነካካ ትምህርታችን አድርባይነታችንን የሚያጥብልን መቼ ይሆን?ሲል ተገረመ።ምሁራዊ ክብራችን ለጊዜው ባለስልጣኖች ሳይንበረከክ፣በትምህርት ያገኘነው ሰብዓዊ ኩራት ለጠመንጃ አፈሙዝ ሳይርገበገብ የምንኖርበት ወቅት ይመጣ ይሆን?ዛሬ በክብርና በሰብዓዊ ኩራት ያበጠው ልቤ ነገ በትልቅ ደሞዝ፣በስልጣንና በቤተሰብ ጫና ተደፍጥጦ ይሟሽሽ ይሆን?ብሎ ሰጋ።

በፕሮግራሙ መሠረት የየክፍሉ ዲኖች ተመራቂ ተማሪዎቻቸውን ያስተዋውቁ ጀመር፤

“ የ…ዲፓርትመነት ዕጩ ምሩቃን በዲግሪ መመረቃችሁን ለማመልከት መነሳንሳችሁን ከቀኝ ወደ ግራ አዙሩ!” ለአጭር ቅጽበት ተፍተፍታ ተሰማ።

“ ከዚህ ቀጥሎ በትምህርታቸው ላቅ ያለ ውጤት ላሳዩ ተማሪዎች…” የተረፈውን አለማየሁ አላዳመጠም፤የሰማው “ አለማየሁ ለማ! ” ሲባልና ከወደቀኝ ጥግ የመጣውን የእናቱን ቃጭል ድምጽ ብቻ ነበር።

ጥቁር ካባውን እያማታ፣የቆቡ መነሳንስ ከእርምጃው እኩል እየተርገፈገፈ በወላጆች ጭብጨባ ታጅቦ ወደ መድረኩ ወጣ።በቀይ ጨርቅ የተለበጠውን ክርታስ ይዞ ሲመለስ አሁንም የእናቱ ዕልልታ ከውካታውና ከጭብጨባው በላይ ጎልቶ ተሰማው።

***

የአለማየሁ እናት ወደ ግራ ዞር ብለው ጥቋቁር ካባዎችና ቆቦች የሞሉትን አዳራሽ እየተመለከቱ አይኖቻቸው በደስታ እንባ እንደተሞሉ ቀስ በቀስ ህሊናቸው የኋሊት ተንሸራተተ…

አለማየሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ት/ቤት ሲወስዱት ከእናቱ መነጠል ተስኖት እዬዬ ማለቱን አስታወሱ።አስተማሪዎችና ተማሪዎች እንደጉድ ይመለከቷቸው ነበር። ሰርከስ እንደሚያዩ ሁሉ ተሰብስበው በደስታ ያውካካሉ።የት/ቤቱ ምክትል ርዕሰ-መምህር ወደ እናት ጠጋ ብሎ፣ “ አሳስተው ይህን ጡት ያልጠገበ ልጅ አስመዘገቡኝ።ምን ያህል እንደሚያስቸግር አሁን ተገነዘቡ አይደል እሜቴ? ” አላቸው።

“ ፈትል ይዤ መጥቼ እዚሁ እየዋልኩ፣እዚሁ እያጠባሁት ይማራል። ”

“ ችክ አይበሉ እሜቴ፣ለሚመጣው አመት ልመዘግበው ቃል እገባለሁ።አሁን ይውሰዱት፤እሱም አይሳቀቅ!”

እናት አላመኑም።ዛሬ ዛሬ ነው፤መጪው ዓመት ደግሞ ሌላ።

“ ለጊዜው ነው ሆዱ የሚባባው፤አሁን ይለምዳል።ደግሞስ ከወንድሙ ጋር አንድ ፈረቃ ቢመደቡልኝ ኖሮ…” አሉ እናት የልጃቸውን ቁንጮ እየደባበሱ።

“ ለርስዎ ስል የመላውን ክፍል ፈረቃ መለወጥ የምችል ይመስልዎታል? አሁን ይውሰዱት፤ጡት ይጥገብ! ”

“ አዎ አልማርም!ጡት አልጠገብኩም!ወደቤት እሄዳለሁ!” አለማየሁ ተንጫረረ።

በቦታው የነበረ ሰው ሁሉ በሳቅ አውካካ፤ተማሪዎችና አስተማሪዎች።እናት ብቻ አልሳቁም።

“ አይዞህ የኔጌታ! እዚሁ አንተው ጋር እውላለሁ።አትፍራ! ”

የአስተማሪዎች አይን እንደጦር እየወጋቸው በስንት ማባበል ወደ ክፍል አስገቡትና በር ላይ ቀረት አሉ።ከእናቱ ተነጥሎ ክፍል ውስጥ መቀመጥ አልሆነለትም።ልቡ ውስጥ ሃያል ጉድለት ተሰማው።ተስፈንጥሮ ወጣ።እናት የመጨረሻ ተስፋቸው ላይ ነበሩ!እናም ትግስታቸው መገባደጃ ላይ።

“ እንግዲህ አለማየሁ ግባና ተማር ብዬሃለሁ!እኔ እዚሁ እጠብቅሃለሁ!” አሉት።የመራር ሽንፈት ዘርፍ ጠንካራ ልባቸውን እየነካካ መራር ስሜት እየወጋቸው ነበር።

“ እማዬ ቆንጆዋ አብረሽኝ ወደ ክፍል ግቢ!” ቀሚሳቸውን ይዞ ሙጭጭ!

አብረውት ገቡ።አብረውትም ተማሩ።

ሁለት ወራት አለፉ።እናቱ እየሄዱ ጡታቸውን ሲያጠቡት፣ታላላቅ መንድሞቹና እህቱ ት/ቤት አድርሰው፣ክፍል አስገብተውት ሲመጡ፣ቀስ በቀስ ሆዱ መባባቱ፣አይኖቹ በእንባ መሞላታቸው እየቀረ መጣ።ቤት ውስጥ ሳሎኑ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ትልቅ የፊደል ገበታ ሲበላም እያነበበ፣ሲወጣም ሲገባም እያነበበበ፣ወንድሞቹን እየጠየቀ የፊደልን ዘሮች ደረጃ በደረጃ አወቀ።መምህራን ት/ቤት ድረስ እናትን አስጠርተው ‘ጡት ያልጠገበ’ ልጃቸውን ርምጃ እንዲያዩ ያደረጉት ከሶስት ወራት በኋላ ነበር።ሞዴል ተማሪ ተባለ።መምህራን ከክፍል ክፍል እያዘዋወሩ፣ጠረጴዛ ላይ አቁመው የአማርኛ መማሪያ መፅሀፍትን ያስነብቡት ጀመር።እናት ልባቸው በኩራት እያበጠ ይህን ሁሉ ተመለከቱ።

በዓመቱ መጨረሻ ሰኔ 30 ሰርተፊኬቱን አንጠልጥሎ እያርገበገበ ሮጦ ወደ ቤት መጣ።ገና የግቢውን በር እንዳለፈ በቀጭን ጨርጫራ ድምጹ፣

“ 49ኛ ወጣሁ!ከ51 ልጅ 49ኛ ወጣሁ! ” እያለ ምድረ ግቢውን አደባለቀው።ትንሽ ቀይ ፊቱ በደስታና በሙቅ ስሜት ተወጣጥራለች።ቁንጮው ቀጥ ብላ ቆማ የምስራቹን የምታበስር ትመስል ነበር።ትልቅ ቁጥር አገኘ፣ከ51 ተማሪዎች 49ኛ!ምናልባትም 1ኛ ቢወጣ ኖሮ ቅር ይለው ነበር።

ታላቅ እህቱ ሰርተፊኬቱን ተቀብላ አነበበችው።ከ51 ተማሪዎች 49ኛ ወጥቷል፣ትክክል ነው።አይኖቿን ወደተቀረው ማመልከቻ ወረወረች።

 

“ አልተዛወረም! ” ይላል።

***

“ አሁን ደግሞ በትምህርታቸው ብልጫ ላሳዩ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን ልዩ ሽልማት እንዲሸልሙልን በትህትና እጠይቃለሁ!” የአለማየሁ እናት ከነጎዱበት አለም ተመለሱ።ሁለመናቸው ጆሮ ሆነ፣ ‘አለማየሁ ለማ’ ሲባል ለመስማት።ሁለመናቸው አይን ሆነ፣ አለማየሁ ለማን መድረኩ ላይ ለማየት።ፀንሰው፣ወልደው፣እያጠቡ እንዳሳደጉትና እንዳስተማሩት ለአንድ አፍታ ተረሳቸው።ጣፋጭ ህልም እያለሙ እንዳይነቁ የፈሩ ያህል ተሰማቸው።

እና… “ አለማየሁ ለማ!” ከእሳቸው እልልታና ከቤቱ ጭብጨባ ጋር አለማየሁ ቀጭን ረጅም ሰውነቱ ላይ የተንጠለጠለውን ካባ እያማታ ወደ መድረኩ አመራ።በአረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ጥብጣብ የተንጠለጠለችውን ክብ ወርቅ አንገቱ ላይ ሲያጠልቁለት ለአንዲት አጭር ቅጽበት ልጅነቱ!ት/ቤቱ!እናቱ ታሰቡት።አንድ ዓመት ከደገመ በኋላ ያሳየው ታላቅ የትምህርት ዝንባሌ፣በየዓመቱ የት/ቤት ኮከብ መሆን፣የእናቱ ያላቋረጠ ፍቅርና ማበረታቻ፣የታላላቆቹ ግፊት፣ያስተማሪዎች ምስጋና…

ከመድረኩ ሲወርድ አይኖቹ በደስታ እንባ ተመልተው፣የጆሮ ግንዱ ደምስር በፍጥነት ሲመታ ተሰማው።አዳራሹን በዕልልታ የሚያቀልጡ እናቱን ሄዶ ጫማቸው ላይ ቢወድቅ፣አቅፎ ጉንጫቸውን፣ከናፍራቸውን፣አይኖቻቸውን፣ጉልበታቸውን፣ሁለመናቸውን ቢስም ተመኘ።በትከሻው ተሸክሟቸው መድረኩ ላይ በመውጣት እሳቸውንም ለሽልማት ቢያቀርባቸው እየተመኘ ለበዓሉ እንዴት አይነት ግሩም መደምደሚያ ይሆን ነበር? ሲል አሰበ።

ወደ ወንበሩ ተመልሶ የወርቋን ሜዳሊያ አንገቱ ላይ እንዳለች ወደ አይኖቹ አስጠግቶ አስተዋላት።የተመለከተው ክብ ወርቅ አልነበረም፤የወተት ጠብታ ነበር።ነጭ የእናት ጡት ወተት ጠብታ…

ጥር 1984

Leave a Comment


nine + = 11