ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ላካሂድ ብትል ተጨባጭ ሁኔታው አይፈቅድላትም

Do you trust Egypt's assurance of NOT declaring war on Ethiopia?
Share your thought
ambasador halilu
አምባሳደር ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሚገኙት የሕግና የኢኮኖሚክስ ፋኩልቲና በፖለቲካል ሳይንስ ኢንስቲትዩት በሕግና በፖለቲካል ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ለፒኤችዲ ሥራቸው በዓባይ ዙሪያ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ለማቅረብ የሚያስችላቸውን ገንዘብ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ከቀረቡ በኋላ የጀመሩትን አቋርጠው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ በሥራ ዓለምም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች ሠርተዋል፡፡ በመጨረሻም በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዓባይ ዙሪያ ለመጻፍ አቅደውት የነበረውን የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ‹‹የዓባይ ውኃ በሕግ ላይ የሚያቀርበው ፈተና›› በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ መጽሐፍ አሳትመው በልዩ ልዩ የአውሮፓ አገሮች ተሸጧል፡፡

ይህንኑ መጽሐፋቸውን በእንግሊዝኛ አስተርጉመው ለንደን ለሚገኘው ጄምስ ኬሪ ለተባለው አሳታሚ ድርጅት ልከዋል፡፡ በአማርኛም ‹‹ለዓባይ ውኃ ሙግት›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ የዚሁ መጽሐፍ አራት ሺሕ ኮፒ ተሸጦ አልቋል፡፡ አሁን የተከሰቱ አዳዲስ ጉዳዮችንና ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበውን ሪፖርት በማካተት መጽሐፉን እንደ አዲስ እንደገና ለማሳተም ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ታትሞ ለገበያ ይቀርባል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት በህዳሴው ግድብ ላይ ያስነሱትን ውዥንብርና ተዛማጅ ጉዳዮችን አስመልክቶ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግብፅ አንዳንድ ፖለቲከኞችና ምሁራን የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በኃይል ጭምር ለማስቆም መንግሥታቸውን እየወተወቱ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የዓባይ ውኃን አስመልክቶ እንደዚህ ዓይነቱን ቀውስ ወይም ነውጥ የመፍጠር እንቅስቃሴዋ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በካይሮ ሬዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም አማካይነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያስችሉ ዜናዎችንና ሀተታዎችን አየር ላይ ታውል ነበር፡፡ ሃይማኖትንም ሽፋን በማድረግ ሕዝብን የሚያነሳሳና የሚቀሰቅስ ተግባር በማከናወን ሰላም እንዳይሰፍን ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም፡፡ ይህ ዓይነቱን የማተራመስ እንቅስቃሴ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስር ‹‹እምቅ የሆነ የግብፅ መከላከያ›› አድርገው ነበር የሚቆጥሩት፡፡

በደርግ ሥርዓት ደግሞ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር ሲደራደሩ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ ጦርነት የምንገባው በውኃ ምክንያት ነው በማለት ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ የደርግ መንግሥት ደግሞ የሶሻሊስት ሥርዓት አራማጅ ስለነበር ግብፅ የምዕራቡ ዓለም ከጐኗ እንዲቆምላት አስችሏታል፡፡ ለዚህም ነው ፕሬዚዳንት ሳዳት ወደ ጦርነት ብንገባ ድጋፍ የሚቸረን እንጂ የሚቃወመን አይኖርም ብለው በመሉ ልብ ለመናገር የደፈሩት፡፡ ሆስኒ ሙባረክ ደግሞ የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ብድርም ሆነ ዕርዳታ እንዳይሰጡ ተፅዕኖ ያደርጉ ነበር፡፡ ፀረ ሰላም ኃይሎችን እያደራጁም ኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ እንዲፈጠር ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ የአሁኑ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲም አንድ ጠብታ ውኃ እንዳይቀነስብን እያሉ ማስፈራራቱን ተያይዘውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንት ሙርሲ ፖለቲከኞችን ጠርተው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያደረጉት ውይይት በሚዲያ በቀጥታ መተላለፉ ስህተት ነበር ይባላል፡፡ በስህተት የተደረገ ነው ወይስ አውቀው ያደረጉት ይመስልዎታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን ስህተት ነው መባሉም እንዲሁም ስህተት ቢሆንም በጣም ነው የሚያስደንቀኝ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ትልቅና በሚስጥር መያዝ የነበረበት ስብሰባ አየር ላይ ማዋሉ ብዙ ትርጉሞች ይኖሩታል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የግብፅ መንግሥት የውስጥ ችግር ስላለበትና ሕዝቡ ይህንን ችግር ችላ ብሎ የትኩረት አቅጣጫውን በዓባይ ላይ ብቻ እንዲሆን ለማድረግ የተወሰደ ዕርምጃ ይመስላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መንግሥት እፎይታ አግኝቶ የራሱን ህልውና እንዲያጠናክር ለማድረግ እንዲያስችለው ሆን ተብሎ የተወሰደ ዕርምጃ ይመስላል፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ በሥጋት ላይ እንድትወድቅ የተደረገም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ በኩል ግን እስካሁን ድረስ በስብሰባው ላይ የተነገረው የግብፅ መንግሥት አቋም ነው ወይም አይደለም አላሉም፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የግብፅ ፖለቲካ ኃይሎች፣ ሚዲያዎችና አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች የሚያራግቡት የጦርነት አዋጅ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ሊያስተጓጉል ወይም ሊገታ እንደማይችል ሊረዱት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የግድቡን ግንባታ በተመለከተ የግብፅ ዋነኛ ሥጋት በምን ላይ ያተኮረ ነው?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ሥጋታቸው የግድቡ ግንባታ አይደለም፡፡ ከግድቡ ጀርባ ነገ ኢትዮጵያ በውኃው የመስኖ ልማት ልታካሂድ ስለምትችል ለዚህም ምንም ዋስትና የለንም የሚል ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሚያቀርቡት ሥጋት ግድቡ ከተሠራ የግብፅ የወደፊት ዕድል በኢትዮጵያውያን ባለሥልጣናት እጅ ይገባል፡፡ ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም በፈለጉ ጊዜ ውኃውን ሊለቁ ካልፈለጉ ደግሞ ሊያቆሙብን ይችላሉ የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥጋት ደግሞ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን የቆየ ነው፡፡ የጥርጣሬ መንፈስ አሁንም እንዳለቀቃቸው ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ ከዚህ ዓይነቱ ሥጋት እንድትወጣ ኢትዮጵያ ያደረገችው ሙከራ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ግብፅን ለማግባባትና ከዚህም ሥጋት እንድትላቀቅ ለማድረግ ብዙ ጥረቶችን አካሂደዋል፡፡ በስድስቱ የተፋሰሱ አገሮች ሕጋዊ ተቋማዊ ማዕቀፍ ለመፍጠር የተደረሰበትን ስምምነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብና የማፀደቅ ሒደቱን ለማዘጋጀት የተደረገው ተግባር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴው ግድብ በግብፅና በሱዳን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር አጣርቶ የሚያቀርብ አንድ ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን እንዲቋቋም መደረጉ፣ ከተከናወኑት ጥረቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይኼው የኤክስፐርቶች ቡድን የህዳሴው ግድብ በግብፅና በሱዳን ላይ የሚያስከትለው ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለ አስታውቋል፡፡

ከቡድኑ መቋቋም በፊትም ኢትዮጵያ ግድቡ ጉዳት እንደማያመጣ ተናግራለች፡፡ የግብፅ ኃይድሮሎጂስቶችም ይህንን በመደገፍ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ነገሩን ሳታከር ጉዳዩን በዲፕሎማሲና በሰላም ለመፈጸም ጥረት ማድረጓ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን እነዚህ ሁለት አገሮች የቡድኑ ሪፖርት ይህንን ውጤት ይዞ ሊወጣ የቻለው ኢትዮጵያ ድንገት የተሟላ መረጃ ሳትሰጥ ቀርታ ሊሆን ይችላል የሚል ሌላ ሥጋት ተፈጥሮባቸዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ምንም ነገር ይሁን ምንም ግብፆች በህዳሴው ግድብ ላይ ፈቃደኝነታቸውን በይፋ የሚገልጹበት ጊዜ መቼም አይኖርም ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፈቃደኛ የማይሆኑት በምን ምክንያት ይመስልዎታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ግብፅ ፈቃደኛ ሆነች ማለት እንደ ዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ የዕርዳታ እጆቻቸውን እንዲዘረጉ ያስችላቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን በሰበብ አስባቡ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀር ነው የሚያደርጉት እንጂ፣ በምንም ሁኔታ ፈቃደኝነታቸውን አያሳዩም፡፡

ሪፖርተር፡- የዓባይ ጉዳይ ሁልጊዜ የሚቀርበው የኢትዮጵያና የግብፅ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ነው፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- የዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያና የግብፅ ብቻ ሆኖ መቅረብ የለበትም ባይ ነኝ፡፡ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ስድስት አገሮች ተቀብለውታል፡፡ በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን ለመግባት እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ እነዚህን አገሮች ስብሰባ በመጥራት በጉዳዩ ላይ ተወያይተውበት ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲጓዙ የማድረግ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጦር ልትሰብቅ ትችላለች ብለው ያምናሉ? ውኃው የእኔ ብቻ ነው አንድም ጠብታ መቀነስ የለበትም የሚል አቋም አላት፡፡ ይህንን እንዴት ይገነዘቡታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- እዚህ ደረጃ ላይ እንኳን አትደርስም፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ላካሂድ ብትል ተጨባጭ ሁኔታው አይፈቅድላትም፡፡ የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ የእኔ ብቻ ነው የሚለው አቋሟ በዓለም አቀፍ ሕግ ዘንድ ቦታ ወይም ተቀባይነት የለውም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በ101 የድምፅ ድጋፍ፣ በሦስት ተቃውሞና በ27 ድምፀ ተአቅቦ ያለፈው የውኃ ኮንቬንሽን የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴው ግድብ በግብፅና በሱዳን ሕዝቦች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጣ መሆኑን ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦችና መንግሥታት በምን መልኩ ማስረዳት ይቻላል ይላሉ?

አምባሳደር ኃይሉ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የጀመረውን በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መንገድ የማስረዳቱን ሥራ ሳይታክት መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጐትጓቾች (ሎቢስትስ) የሚባሉ አሉ፡፡ እነኚህ ጎትጓቾች ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ በቅጥር የሚታቀፉ የውጭ አገር ዜጐችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በመገናኛ ብዙኅንም ሆነ በሌላም መስክ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የምትከተለው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም ወገኖች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ፣ ምንም ጉዳት አያመጣም የሚለውን በደንብ አድርገው የማስተጋባትና የማስረዳት ሥራ እንዲያከናውኑ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የቡድኑ ሪፖርት ከመቅረቡ በፊት ወንዙ የፍሰት አቅጣጫውን ቀይሮ እንዲሄድ የማድረጉ ሥራ ግብፅን ያበሳጨ ይመስላል፡፡

አምባሳደር ኃይሉ፡- ይኼ እኮ አንዳንዴ መሐንዲሶች የሚወስኑት ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያም የወንዙን አቅጣጫ ያስቀየረችው ቀደም ሲል ያስጠናቸው ጥናት በግብፅና በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል አስቀድማ በማረጋገጧና ይህንንም ለሁለቱ አገሮች ቀደም ብላ በማሳወቋ ነው፡፡ ሪፖርቱም ቢሆን እንደሚደግፋት በማረጋገጧ ነው፡፡ በተረፈ ግን ግብፅ ሰበብ የምታበዛበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ግድቡን ከገነባች በኋላ የግብፅ ዕጣ ፈንታ በኢትዮጵያ ሥር ይወድቃል በሚል ነው፡፡ ይህንን እንዴት ዝም ብለን እናያለን የሚል የተሳሳተ እምነትና ጥርጣሬ ስላደረባት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግብፅን ሕዝብ ጉዳት ላይ የሚጥል ነገር ፈጽሞ አትሠራም፡፡ አታደርግምም፡፡ ነገር ግን የግብፅ መንግሥት ይህንን ለመቀበል አሻፈረኝ ያለው፣ የግድቡ ሥራ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ያለምንም ችግር ለግንባታው ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ልታገኝ ትችላለች በሚል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ግብፅ ነገ ተነስታ የቡድኑ ውጤት በጣም ግሩም ነው፣ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲህ ያሰበችውን ግንባታ ትፈጽም ለማለት ፈጽሞ አትደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ በቅርቡ በተከናወነው የአፍሪካ መሪዎች 21ኛው ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ጥሩ አቀባበል አልተደረገላቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መቀበል ሲገባቸው የተቀበሏቸው የማዕድን ሚኒስትሯ ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ ናቸው፡፡ በስብሰባውም ላይ ፊት መቀመጥ ሲገባቸው አምስተኛ ረድፍ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ የግብፅን ክብር አሳንሳለች እያሉ ግብፆች ያማርራሉ፡፡

አምባሳደር ኃይሉ፡- ይኼን ምሬት እንኳን አልሰማሁም፡፡ በስብሰባው ላይ ግን ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ለፕሬዚዳንቱ የተሟላ አቀባበል አልተደረገላቸውም የሚለው ምክንያት ለመፍጠር ነው እንጂ ከዲፕሎማሲም አኳያ ሲታይ ተገቢ ወቀሳ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉንም አገር መሪዎች ተቀባይ ነች፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እያንዳንዱን መሪ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ይቀበሉ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ብቻ መሸፈን ወይም ዳር ማድረስ ይቻላል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- አንችልም፡፡ እስካሁን እኮ ከሕዝብ የተሰበሰበው ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ቢጠጋ ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ወጪ የሚጠይቀው ደግሞ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ያህል ገንዘብ ለማዋጣት ያዳግተናል፡፡ ለዚህ ነው ግብፅ የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ተቀብያለሁ ብላ ካረጋገጠች፣ ወዲያውኑ ኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታ ታገኛለች የሚል አመለካከትና እምነት ስላላት ነው ለማደናቀፍ ደፋ ቀና የምትለው፡፡ ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ቢውል ግን ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ግብፅና ሱዳንም የጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ፡፡ እነሱ ግን ይህ በጎ ጐኑ አይታያቸውም፡፡ የግብፆች ትልቁ ጥርጣሬያቸው ኢትዮጵያ በሕዝቡ መዋጮ ብቻ የግድቡን ግንባታ የማጠናቀቅ ወይም ዳር የማድረስ አቅም ስለሌላት፣ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ከሌሎች አገሮች በስውር ዕርዳታና ብድር ልታገኝ ትችላለች የሚል ነው፡፡

ስለሆነም ይህንን ለማጨናገፍ ሲሉ የማስፈራራት ዘመቻ እያካሄዱ ነው፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት መልዕክተኞቻቸውን ወደተለያዩ አገሮች በመላክ የማግባባት ሥራ እያካሄዱ ስለመሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ደቡብ ሱዳን እንኳን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዳትቀበል ወይም እንዳትፈርም ብዙ ተፅዕኖ አድርገውባት ነበር፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐንም እንዲሁ አግባብተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ የምታካሂደው ይህ ዓይነቱ ቅስቀሳ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አለው ይላሉ?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ተቀባይነት የለውም፡፡ አይኖረውምም፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለንበት 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በውይይት መፍታት፣ ሰጥቶ መቀበልና በልዩነት ተቻችሎ መኖር እንጂ የጦርነት አዋጅ፣ በጠመንጃና በማስፈራራት የሚፈጸም ነገር አለመኖሩን በተግባር እያየን ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓባይን ግድብ አስመልክቶ እስከዛሬ ድረስ ያካሄዳቸው የማግባባትና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሁሉ በጣም ጥሩና የሚደገፉ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በዲፕሎማሲ እንዲያልቅ የምናደርገው ጥረት በአቋማችን ያለማመን መስሎ እንዲታይብን ደግሞ አንፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ከግብፅ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መካከል የቀድሞው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አልባራዳይ ኢትዮጵያን ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሰዋል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ሚስተር አልባራዳይ ይህንን ጥያቄ ሊያቀርቡ ወይም ይህንን ዓይነት አቋም ሊያሳዩ የቻሉት በዓለም አቀፍ ሕግ በጣም የዳበሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያም በበኩሏ የግብፅን ሕዝብ ካይሮ በሚገኘው አምባሳደሯ አማካይነት ማስረዳት ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት ሲሰማ የቆየው ኢትዮጵያ እኛን ለመጉዳት ወይም ለማጥቃት ስትል ነው ይህን ግድብ ለመገንባት መንቀሳቀስ የጀመረችው የሚለውን ብቻ ነው፡፡ የግብፅ ሕዝብ አሁን ከተደቀነበት የውስጥ ችግር በመነሳት በጣም የሚያስተባብረው የዓባይ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የማግባባት ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ ታስቦ የነበረውም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መቀጠል አለበት፡፡ የግብፅ ልዑካን እንደመጡ ሁሉ የእኛም ልዑካን ወደ ግብፅ ማቅናት አለባቸው፡፡ አሁን ግን ጉዳዩ እየከረረ ስለመጣ ልዑካኑን ማንቀሳቀሱ ጊዜው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፀጥታ ኃይሎች ተከቧል ይባላል፡፡ ለምን ይሆን?

አምባሳደር ኃይሉ፡- ይህ ጉዳይ በሁለት መልኩ መታየት ይኖርበታል፡፡ አንደኛው የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በተመለከተ መላው የግብፅ ሕዝብ ተቃውሞ አስነስቷል እያሉ ኢትዮጵያ እንድትደናገጥ ለማድረግ ሆን ተብሎ የተወሰደ ዕርምጃ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅን የዓለም አቀፍ ሕግ ስለሚያስገድዳት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከግብፅ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል አንዳንዶቹና ፖለቲከኞች በስዊዝ ካናል በኩል የሚያልፉ የኢትዮጵያ ዕቃዎች እንዲታገዱ መንግሥታቸውን እየወተወቱት ነው ይባላል፡፡

አምባሳደር ኃይሉ፡- ስዊዝ ካናል ዓለም አቀፍ የመተላለፊያ መስመር ነው፡፡ አሁን ይህንን ተግባር ይፈጽማሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ በእርግጥ ከዓመታት በፊት ከእስራኤል ጋር ባካሄዱት የስድስቱ ቀናት ጦርነት ወቅት ካናሉን ዘግተው ነበር፡፡ አሁን ግን ምንም ዓይነት ጦርነት አይካሄድም፡፡
Source: Ethiopian reporter

Leave a Comment


+ 8 = seventeen