
የኢሚግሬሽን ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አይደለም በዚህም ለእንግልት እየተዳረግን ነው የሚሉና መሰል አቤቱታዎች በተገልጋዩ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎች ናቸው፡፡
ተቋሙ የችግሩ መንስኤዎች የህግ ወጥ የደላሎች መበራከትና አሁን ካለው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ለዚህም ያካሄድኳቸው ግምገማዎችና ክትትሎች ማሳያ ናቸው ብሏል፡
የዋናው መምሪው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀይለ ጊዮርጊስ እንደሚሉት አዲስ አበባ በሚገኘው ዋናው ተቋም የሚስተዋለው የአገልግሎት መጨናነቅ ህገውጥ ደላሎች ለፓስፖርት ፍላጊዎች በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል፡፡
“በክልሎች ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት መስሪያ ቤቶች ቢኖሩም ህገወጥ ደላሎቹ ተጨማሪ ብር ለማግኘት ትክክለኛው ፓስፖርት ያለው አዲስ አበባ ነው በማለትና ተገልጋዩን ቪዛ እናመጣላችዋለን እያሉ ፓስፖርታቸውን እየቀሙ ይወስዳሉ ” ብለዋል፡፡
በህገወጥ ደላሎችና በአንዳንድ የተቋሙ ሰራተኛች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥቅም ትስስርም ሌላኛው የችግሩ መንስኤ መሆኑን ነው አቶ ጌታቸው የሚገልጹት፡፡
“ህገወጥ ደላሎቹ ከሰራተኛቹ ጋር በመመሳጠር ባለጉዳዮቹን ፓስፖርት የሚወስዱበትን ጊዜ ለማሳጠር እንዲሁም ገንዘብ ከከፈሏቸው ፓስፖርተ የሚወሰድበትን ቀጠሮ እናሳጥርላቸዋለን በማለት የተቋሙ አንዳንድ ሰራተኛችም ከተገልጋዮች ግቦ እየተቀበሉ ከደላሎች ጋር አላስፈላጊ ድርጊቶችን በመፍጠር አግልግሎቱን ሲያዛቡ የነበሩ ናቸው “ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተቋሙ የሚስተዋለውን መጨናነቅ በመፍታት ለተገልጋዩ ፈጣና አገልግሎት ለመስጠት ተቋሙ በቂ ጥናት በማድረግ ህጋዊ እርምጃዎችን እየወሰደ እንዳለ ገልጸዋል ዳይሬክተሩ፡፡
“እነዚህ የስነምግባር ችግር የታየባቸው ሰራተኛ በአንዳንዶቹ ላይ አስተዳደራዊ እርምጅ በሌሎቹ ላይ ደግሞ ወደህግ የመውሰድ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በዚህም ረገድ አዋሳ ከተማ በሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት አስራ አንድ ሰራተኛ ላይ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ በማውጣት በቁጥጥር እንዲውሉ ተደርጓል” ብለዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ተቋሙ የተጀመረውን አዲስ አሰራር ተከትሎ አዲስ አበባ በሚገኘው ይሰጥ የነበረው የስድስት ወር ቀጠሮ ወደ ሁለት ወር ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተለይ መንግስት ተቋም የሚሰሩ ሰራተኛ የመስሪያ ቤት ደብዳቤ ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ የሚስተናገዱበት አሰራርም እየተዘረጋ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በቀጣይም ሁሉንም ተገልጋዮች በአንድ ቀን ውስጥ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ቅርንጫፎቹን ማስፋት፣ በቂ የሰው ሀይል የሟሟላትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በፓስፖርት ፈላጊዎች ላይ እንግልት በመፍጠር ላይ የሚገኙ ህገወጥ ደላሎችና ሰራተኛ በማጋለጥ ተቋሙ የጀመረውን አሰራር በመደገፍ ረገድም ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን በመጠቆም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ertagov.com
Join Conversations