በአገራችን የመሰረተ ልማት ተግባሮችን የሚያቀናጅ ተቋም ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 6 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘረጉ የመሰረተ ልማት ተግባሮችን የሚያቀናጅ ተቋም ሊቋቋም ነው።

በብዛት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሲከናወኑ አንዱ ተቋም የሰራውን ሌላው ተቋም  የራሱን በሚሰራበት ወቅት የሚያበላሽበት ምክንያት ስራዎችን በጋራ ካለመስራት የመነጨ መሆኑን ነው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የሚናገረው።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃደ ሃይሌ እንደሚሉት ፥ የተጠናቀቁ መንገዶች ዳግም እንዲቆፈሩ ፤ የመንገድ ልማት ሲከናወን ሌሎች ችግሮች የመፈጠራቸው ምክንያት የመሰረተ ልማት የሚዘረጉ ተቋማት እርስ በርስ መናበብና በቂ መረጃ መለዋወጥ ባለመቻላቸው ነው።

በስራ አስኪያጁ ሃሳብ የሚስማሙት የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድም ለቴሌኮም አገልግሎት መቋረጥ ግንባታዎች አንድ ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ።

የስራ ሃላፊዎቹ እንደሚሉት ፥ የመንገድ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት በርካታ መታሰብ ያለባቸው ቁም ነገሮች አሉ፤ ቀደም ሲል በቦታው የተዘረጉ የአገልግሎት መስመሮች መኖር አለመኖራቸው ፤ ከሌሉም በአንድ ጊዜ መገንባት የሚችሉበት አግባብ መኖር አለመኖሩ ፤ በመሰረተ ልማቶቹ ዝርጋታ ወቅትም ህብረተሰቡ የአገልግሎት መቋረጥ እንዳይገጥመው ማድረግ ስለሚቻልባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እርስ በእርስ ምምከር ያስፈልጋል።

አሁን የከተማዋን እድገት ተከትሎ ለመጣው ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የነበሩ ችግሮች የማይቀጥሉ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት የሚለው የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ፥ ችግሩን ለመቅረፍ በፌዴራል ደረጃ የመሰረተ ልማት የቅንጅት ግብረ ሃይል መቋቋሙን የገለፀ ሲሆን ፥ ተቋሙ ተቋቁሞ በዚህ አመት ስራ ይጀምራልም ነው ያለው።

በሚኒስቴሩ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ የፕሮጀክት ስራ አመራር ዳይሬክተርና የግብረ ሃይሉ አባል አቶ ጥዑመዕዝጊ በርሄ እንዳሉት ፥ ግብረ ሃይሉ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወቅት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የሀብት ብክነት ለመከላከል የሚችልባቸውን ሰነድ ከችግሮቹ በመነሳት አዘጋጅቷል።

አንዱ የሰራውን ሌላው ተቋም የራሱን ሲገነባ በሚንድበት ወቅት ህብረተሰቡ የአገልግሎት መቋረጥ ይደርስበታልና ፤ ግብረ ሃይሉ እነዚህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተቋማት ተቀናጅተው እንዳይሰሩ ያደረጋቸውን ምክንያትም ለይቷል በጥናት ሰነዱ ።

አቶ ጥኡመዝጊ እንዳሉት፥  የሚቋቋመው ተቋም ተቋማቱ እቅዳቸውን በተናበበ መልኩ በጋራ እንዲያዘጋጁ  ከመደገፍ ባለፈ በግንባታ ወቅት የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠርና የስራ መጓተት እንዳይከሰት ክትትል ያደርጋል።

በተጨማሪም በቀጣይ አንድ ተቋም ማንኛውንም መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ሲያስብ ወደ ተቋሙ በመምጣት የተቋሙን ፍቃድና አቅጣጫ ማግኘት የሚኖርበት ሲሆን ፥ ተቋም ባደጉት ሀገራት እንደሚደረገው የመሰረተ ልማት ማስተር ፕላን በማዘጋጀትም ስለ እያንዳንዱ መሰረተ ልማት ሙሉ መረጃን የሚይዝ ይሆናል።

Source: Fana BC

Leave a Comment


one + 4 =